አርባምንጭ ከተማ ወደ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ወረደ - ኢዜአ አማርኛ
አርባምንጭ ከተማ ወደ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ወረደ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 36ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ።
በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ፋሲል ከነማ አርባምንጭ ከተማን 2 ለ 0 ረትቷል።
ታምራት እያሱ ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ውጤቱን ተከትሎ በሊጉ 15ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው አርባምንጭ ከተማ በ35 ነጥብ ሁለት ጨዋታዎች እየቀሩት የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃ ይዞ ከፕሪሚየር ሊጉ መውረዱ የተረጋገጠ የመጀመሪያው ክለብ ሆኗል።
በዘንድሮው የውድድር ዓመት አራት ክለቦች ከሊጉ ይወርዳሉ።
ተከታታይ ድሉን ያስመዘገበው ፋሲል ከነማ በበኩሉ በ52 ነጥብ ደረጃውን ከስድስተኛ ወደ አራተኛ ከፍ አድርጓል። በሊጉም 13ኛ ድሉን አስመዝግቧል።
የፋሲል ከነማው ታምራት እያሱ በሊጉ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ወደ 14 ከፍ በማድረግ ተመሳሳይ ግብ ካላቸው የሲዳማ ቡናው አቤል ያለው እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ናትናኤል ዳንኤል ጋር በጋራ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን መምራት ጀምሯል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወላይታ ድቻን 2 ለ 1 አሸንፏል።
በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ በረከት ወልደዮሐንስ እና አቤል ሀብታሙ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ያሬድ ዳርዛ ለወላይታ ድቻ ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ከአራት የሊጉ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ50 ነጥብ ከነበረበት ስምንተኛ ደረጃ ወደ አምስተኛ ከፍ ብሏል።
በውድድር ዓመቱ 12ኛ ድሉን አግኝቷል።
በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ ዘጠነኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ወላይታ ድቻ በ47 ነጥብ ከነበረበት 7ኛ ደረጃ ወደ 8ኛ ዝቅ ብሏል።