ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው በእውቀትና በክህሎት የበለጸገ የሰው ሃይል በማፍራት ረገድ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ ነው

ደሴ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፡- የወሎ ዩኒቨርሲቲ በእውቀትና በክህሎት የበለጸገ የሰው ሃይል በማፍራት ረገድ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

ዩኒቨርሲቲው የተግባር ተኮር ትምህርትን ውጤታማ ለማድረግ የቀረጻቸው የስርዓተ-ትምህርት ፕሮግራሞች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ  ነው።


 

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አወል ሰይድ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንደገለፁት፣ ዩኒቨርሲቲው ተግባር ተኮር ስርዓተ ትምህርትን ውጤታማ ለማድረግ መሰረተ ልማትና ግብዓት ማሟላት ላይ በትኩረት እየሰራ ነው።

ለዚህም በጥናት በለያቸው 44 ፕሮግራሞች  ላይ የሚመክር መድረክ  ዛሬ በማዘጋጀት ግብዓትን በማሰባሰብ አዳብሮ በ2019 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራው  ላይ ለመተግበር ማለሙን ጠቁመዋል።

የፕሮግራሞቹ ትግበራም በእውቀትና በክህሎት የበለጸገ የሰው ሃይል በማፍራት ረገድ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እንደሚያግዙት  አረጋግጠዋል።

ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራቱን በማስጠበቅ ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት አዎንታዊ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ትውልድ ለመገንባት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በዩኒቨርሲቲው የጢጣ ልዕለ ህክምና ካምፓስ የፋርማሲ ትምህርትና አገልግሎት ትምህርት ክለሳ ኮሚቴ ሰብሳቢ አድማሱ አሰን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ተግባር ተኮር ትምህርትን እውን ለማድረግ የፕሮግራም ክለሳ ተካሄዷል።

በጤናው ዘርፍም አገልጋይነትን የተላበሰ ባለሙያ በማፍራት ጤንነቱ የተጠበቀ፣ አምራች፣ ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ለመፍጠር እንደሚያስችልም አስገንዝበዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ድንኳና ንጉሣ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ ብቁ የሰው ሃይል ለማፍራት መሰረታዊ ጉዳይ በመሆኑ በትኩረት እየተሰራ  ነው ብለዋል።


 

በዩኒቨርሲቲዎች የተጀመሩ ማሻሻያዎች የትምህርት ስርዓቱን ተግባር ተኮር ማድረግና ለጥራት ትኩረት በመስጠት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እየተሰራ ነው ያሉት።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም