የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ችግርን ለማቃለል በቅንጅት መስራት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ችግርን ለማቃለል በቅንጅት መስራት ይገባል
ባህር ዳር፤ ሰኔ 15 /2018 (ኢዜአ)፡-የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ለማቃለል በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አመለከተ።
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲና የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በመተባበር "የዓለም የምግብ ቀንን" ዛሬ በባህር ዳር ከተማ አክብረዋል።
በዩኒቨርሲቲው የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ስራ አስፈጻሚ በቃሉ ውብሸት (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ የስነ- ምግብ ጉዳይ የባለድርሻ አካላትን ቅንጅትና ትብብር የሚጠይቅ ነው።
ዩኒቨርሲቲውም የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚያስከትለውን ጉዳት ቀድሞ በመገንዘብ ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራትና በዘርፉ ምርምሮችን በማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከዚህ ውስም የግብርናውን ዘርፍ በመደገፍ የሰብል ምርቶች በዓይነትና በብዛት እንዲመረቱ በማድረግም ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
የመድረኩ ዋና ዓላማም የምርምር ስራዎችን አጠናክሮ ከማስቀጠል ባለፈ በምግብ እጥረት የሚመጡ የጤና ችግሮችን ለማቃለል የተሻሉ ስራዎችን ለመስራት ያለመ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ በምርምር የታገዘና መረጃን መሠረት ያደረጉ ችግር ፈቺ የፖሊሲ ምክረ-ሀሳቦችን በማቅረብ የጤና ችግሮች እንዲፈቱ እየሰራ ይገኛል።
በክልሉ የህጻናት መቀንጨር ችግርን ለመቅረፍም ከምርት ጀምሮ እስከ አመጋገብ ያለውን ችግር ለመፍታት ግንዛቤ ፈጠራ ላይ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
እንደ ሀገር በግብርናው ዘርፍ የተያዘውን በምግብ ራስን የመቻል ግብ ለማሳካት የምርምር ስራዎችን በማስፋት ማከናወን እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።
የስርዓተ-ምግብ ጉዳይ የተፈጥሮና የሰብዓዊ መብት ጉዳይ በመሆኑ፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ መንግስታዊና ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ችግሩን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ሁሉ እገዛ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።
በመድረኩ ላይም የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አመራሮች፣ ተመራማሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።