አረንጓዴ ዐሻራ ለኢትዮጵያ ታላቅ ክብር እና ተሰሚነት አጎናጽፏታል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
አረንጓዴ ዐሻራ ለኢትዮጵያ ታላቅ ክብር እና ተሰሚነት አጎናጽፏታል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦ አረንጓዴ ዐሻራ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ረገድ ለኢትዮጵያ ታላቅ ክብር እና ተሰሚነት ማጎናጸፉን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ አረንጓዴ ዐሻራ በተባበሩ ክንዶችና በመደመር የከበረ እሳቤ የመስራት ምስክር ነው ብለዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሠራተኞች ጋር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በጫካ ፕሮጀክት ዛሬ መካሄዱንም ጠቁመዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ እንደ ሀገር የውበት ምንጭ የኢኮኖሚ ተደማሪ አቅም ይሆናል ተብሎ ታቅዶ የተሠራና በውጤት ፍሬ አፍርቶ እየታየ ያለ ተግባር መሆኑን አመልክተዋል።
ይህ በተግባር የተደገፈ ግዙፍ የአረንጓዴ ልማት ጉዞ፣ ከኢኮኖሚያዊና የአካባቢ ጥበቃ ፋይዳው አልፎ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ረገድ ለሀገሪቷ ታላቅ ክብር እና ተሰሚነት አጎናጽፏታል ነው ያሉት።
የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት በከፍተኛ ሁኔታ በመሳብ ላይ የሚገኘው ይህ ስኬት፣ የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን (COP32) በኩራት ለምታስተናግደው ታሪካዊ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ጠንካራና አስተማማኝ መሰረት መጣሉን ተናግረዋል።
ይህ ሁለንተናዊ እመርታ የመንግሥትንና የዜጎችን ትጋት የሚያሳይ፣ መላው ኢትዮጵያውያንን እጅግ ሊያኮራ የሚገባ ታላቅ ሀገራዊ ድል ነው ብለዋል።
በዚህ ዓመት "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሀሳብ 8 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ያቀድነውን ግብ ለማሳካት በኅብረት እንትከል፣ እንንከባከብ ሲሉም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።