ቀጥታ፡

የአረንጓዴ ዐሻራ የኢትዮጵያን ስምና ዝና በዓለም አደባባይ ከፍ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የግብርና ምርታማነትን በማሳደግና በዲፕሎማሲው መስክ የኢትዮጵያን ስምና ዝና በዓለም አደባባይ ከፍ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አመራርና ሠራተኞች ጋር በየካ ተራራ የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሂደዋል።


 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ በየዓመቱ የሚካሄደው የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢ ባህል እየሆነ መጥቷል ብለዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የግብርና ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር በዲፕሎማሲው መስክ የኢትዮጵያን ስምና ዝና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ በማድረግ ጉልህ ፋይዳ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ተግባራዊ ስራ እያከናወነች የምትገኝ ሀገር መሆኗን ለዓለም በማሳየት ተሰሚነቷንና ተደማጭነቷን ያጎለበተ ብሔራዊ የልማት ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።


 

የውሃ ሃብት አቅምን በማሳደግና ከገፀ ምድር የነጠፉ ሐይቆች መልሰው እንዲያንሰራሩና የውሃ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ዕድል እየፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል።

በደን ሃብት መመናመን ሳቢያ የሚፈጠርን የአፈር መሸርሸር በማስቀረትም ከፍተኛ ጠቀሜታ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።

በሌማት ትሩፋት የፍራፍሬ ልማት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና በሁሉም የግብርና ዘርፎች ምርታማነትን በማሻሻል የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አብራርተዋል።

የዝናብ መጠንን በማሻሻልም ክረምት ከበጋ ለግብርና ሥራ መሳለጥ አይነተኛ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።


 

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኝ መትከሏን በማንሳት፥ ዘንድሮም ተስፋን እንትከል በሚል መሪ ሀሳብ 8 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል በበቂ ዝግጅት ወደ ሥራ መገባቱን አንስተዋል።

የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በተያዘው ዕቅድ መሠረት ለማሳካት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም