የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር በርሃም ሳሊህ (ዶ/ር)ን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ውይይቱን አስመልክቶ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር በርሃም ሳሊህ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ከፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ውይይቱ ኢትዮጵያ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞችን በማስተናገድ ረገድ ለምትጫወተው ወሳኝ ሚና ድርጅታቸው ያለውን አድናቆትና እውቅና ለመግለጽ ትልቅ አጋጣሚ መፍጠሩን ገልጸዋል።
በተለይም ሀገሪቱ ስደተኞችን በብሔራዊ ሥርዓቱ ውስጥ ለማካተትና በሰብአዊ እርዳታ ላይ ብቻ ጥገኞች እንዳይሆኑ ለመርዳት በቅርቡ ይፋ ያደረገችውን የማካተት ፍኖተ ካርታን በአብነት ጠቅሰዋል።
በፍኖተ ካርታው የትግበራ ሂደት ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ያረጋገጡ ሲሆን፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም የጋራ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል፣ ኮሚሽነር በርሃም ሳሊህ ኢትዮጵያ በቅርቡ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በስኬት በማጠናቀቋ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል።