ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የፕሮጀክት ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) የፌዴሬሽኑን አሰራርና መረጃ አያያዝ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማዘመንና በጋራ ለመስራት የሚያስችል የፕሮጀክት ስምምነት ተፈራርመዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን ፌደሬሽኑ ዘመናዊ የምዝገባ ሥርዓትን በመዘርጋትና ተቋሙን ዲጂታላይዝ በማድረግ ረገድ ብዙ መሥራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

በስምምነቱ መሰረት በቴክኖሎጂ የዳበረ ተቋም ለመገንባት ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) በትብብር እንደሚሰራ ተናግረዋል።




ፕሬዝዳንቱ አያይዘውም ፈጣንና ቀልጣፋ የአትሌቶች አገልግሎት ለመስጠት በጋራ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) የኢንፎርሜሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃኒባል ለማ፤ አትሌቲክስ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ያኮራ ታላቅ ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል።

የፌዴሬሽኑ የዲጂታል ሉዓላዊነት (Digital Sovereignty ) ለማጠናከር ፣ ከዓለም አትሌቲክስ ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖረው የሚያስችል የቴክኖሎጂ ትስስርን ጨምሮ አስፈላጊው ሁሉ ለማድረግ ተቋማቸው ለአትሌቲክሱ እድገት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

ስምምነቱ ከስልጠና ማዕከላት ጀምሮ ፕሮጀክቶችን፣ ክለቦችን እና ተቋማትን ያቀፈ የአትሌቶች ምዝገባ ሥርዓትን የሚዘረጋ ሲሆን፤ የውድድሮችን የአደረጃጀትና የአመራር (ማኔጅመንት) ሥርዓት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው።



ከአትሌቶች አገልግሎት ጋር የተያያዙ የኤምባሲ ጉዳዮችን ከእጅ-በእጅ (ማኑዋል) አሰራር ወደ ዲጂታል ሥርዓት የሚቀይር በመሆኑ፣  ይደርስ የነበረውን እንግልት እንደሚያስቀርም ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

በተጨማሪም ስምምነቱ የፋይናንስ፣ የንብረት አስተዳደር እና የግዥ ሥርዓቶችን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የሚያስችል ሲሆን፤ የፌዴሬሽኑን ድረ-ገጽ (ዌብሳይት) ማበልጸግን ጨምሮ በርካታ የዲጂታላይዜሽን ሥራዎችን የሚያካትት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም