ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እና የዩናይትድ ኪንግደም ግንኙነት ይበልጥ ሊጠናከር ይገባል-ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የኢትዮጵያና የዩናይትድ ኪንግደም ታሪካዊ ትስስር ይበልጥ እንዲጠናከር ጥሪ አቅርበዋል።

በለንደን ከተማ የሲዳራ ግሩፕ (Sidara Group) ያዘጋጀው እንዲሁም በሌበር አፍሪካ ኔትወርክ (Labour African Network) እና በኢትዮጵያ የዩናይትድ ኪንግደም ኤምባሲ በጋራ በተሰናዳው የዲፕሎማቲክ እራት መርሐ ግብር ተካሄዷል።


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት እንዲሁም የዕድገትና ብልጽግና አዳዲስ ዕድሎችን ለመጠቀም የውይይት እና የትብብር መድረኮች ወሳኝ ሚና አላቸው።

የኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ኪንግደም ግንኙነት በመንግሥት ተቋማት መካከል ብቻ የተገደበ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ትብብሩ በንግድ ድርጅቶች፣ በትምህርት ተቋማት፣ በዲያስፖራ ማህበረሰቦች እና በሁለቱ ሀገራት ዜጎች መካከል ባለው ዘላቂ ትስስር ላይ የተመሠረተ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትም ለጠንካራ እና ዘላቂ አጋርነት ዋነኛው ምሰሶ ነው ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የኢትዮጵያን ወቅታዊ የሪፎርም አጀንዳ እና የረጅም ጊዜ የልማት ትልሞችን አንስተዋል።

በተለይም ኢኮኖሚውን ለማጠናከር፣ ለወጣቱ ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንዲሁም አካታች እና ዘላቂ ዕድገትን ለማስፈን እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን አንስተዋል።


 

የኢትዮጵያን ሕዝብ የአይበገሬነት አቅምና በመላ ሀገሪቱ እየታየ ያለውን አዲስ የተስፋ መንፈስ በመጥቀስም የወደፊቱ ጊዜ ብሩህ እንደሚሆን ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል በንግድ፣በኢንቨስትመንት፣በትምህርት፣ በምርምር፣ በቴክኖሎጂ፣ በፈጠራ (ኢኖቬሽን) እና በአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም አቅም ዙሪያ ሰፊ የትብብር ዕድሎች መኖራቸውን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበ የመጣውን ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ በአግባቡ ለመወጣት እና ለሁለቱም ሀገራት ዜጎች ተጨባጭ ጥቅሞችን ለማስገኘት ጠንካራ ዓለም አቀፍ አጋርነት መፍጠር አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑንም አሳስበዋል።


 

የሌበር አፍሪካ ኔትወርክ (LAN) ሊቀመንበር ኤርነስት አምቤ በንግግራቸው ኔትወርኩ፤ የአፍሪካ ድምጽ በዩናይትድ ኪንግደም የፖሊሲ ቀረጻ፣ የንግድ እና የዲፕሎማሲ መድረኮች ላይ ጎልቶ እንዲሰማ በማድረግ ረገድ የተጫወተውን ጉልህ ሚና አድንቀዋል።

አያይዘውም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከአፍሪካ ትላልቅ እና ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ገበያዎች አንዱ መሆኑን በልዩ ሁኔታ አንስተዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ አምባሳደር ብሩክ መኮንን በበኩላቸው፥ የዲፕሎማሲ ሁነቱ እየተጠናከረ የመጣው የሀገራቱ የንግድ፣የኢንቨስትመንት እና ኢኖቬሽን ትብብር ለማስፋት መልካም አጋጣሚን መፍጠሩን ገልጸዋል።


 

ዩናይትድ ኪንግደም ከኢትዮጵያ እና ከአጠቃላይ አፍሪካ ጋር ያላት የኢኮኖሚ አጋርነት ማደግ አዳዲስ ዕድሎችን፣ የጋራ ብልጽግናን እና አካታች ዘላቂ ዕድገትን ለማምጣት እንደሚያስችል መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም