ቀጥታ፡

ብልፅግና ፓርቲ በምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት ቃል የገባቸውን ተግባራት ለመፈጸም በሚያደርገው እንቅስቃሴ የበኩላችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል

ጅማ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦ ብልፅግና ፓርቲ በምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት ቃል የገባቸውን ተግባራት ለመፈጸም በሚያደርገው እንቅስቃሴ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የጅማ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትላንትናው ዕለት ይፋ ባደረገው የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት፣ ብልፅግና ፓርቲ በአብላጫ የምርክ ቤት መቀመጫ ማግኘቱ ይታወቃል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ታመነ ኃይሉ፤ ፓርቲው የጀመራቸውን ትልልቅ ፕሮጀክቶችና በምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት ቃል የገባቸውን ተግባራት ለመፈጸም በሚያደርገው እንቅስቃሴ የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ፓርቲው ከዚህ ቀደም ያከናወናቸው ሰው-ተኮር ልማቶች አገሪቱን ከድህነት ለማውጣት ከፍተኛ አቅም ማበርከታቸውን የጠቀሱት አቶ ታመነ፤ በቀጣይም ልማትን አጠናክሮ ለማስቀጠል በሚደረገው ርብርብ ሕዝቡና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በጋራ ይሰራሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሙደሲር መሐመድ በበኩላቸው፤ ፓርቲው ያቀዳቸውን ግዙፍ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ አጠናቆ ለሕዝብ ተጠቃሚነት ለማዋል ከታችኛው መዋቅር ጀምሮ ሙስናን የመታገል ተግባሩን ማጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል። 

ለዚህም የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን አሰራር በዲጂታል ቴክኖሎጂ ማደራጀት፣ የሙስና መከላከያ ስልቶችን ይበልጥ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የአገርን ሰላም ማስከበርና ልማትን ማፅናት ለመንግሥት ብቻ የሚተው አይደለም ያሉት አቶ ሙደሲር፤ ጉዳዩ የዜጎችን ንቁ ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ እሳቸውም የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

ሕዝቡ በምርጫ ሥልጣን የሰጠው ፓርቲ የገበያ መረጋጋትን ለመፍጠርና ሕገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል የሚያደርገውን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የገለጹት ደግሞ አቶ መልካሙ ቡላ እና አቶ በፀጋው አበራ ናቸው።

አስተያየት ሰጪዎቹ የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ማንኛውንም ጥረት በንቃት በመደገፍ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም