አዲስ አበባ በኮሪደርና በወንዝ ዳርቻ ልማት እንደ አዲስ ነው የተወለደችው - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ በኮሪደርና በወንዝ ዳርቻ ልማት እንደ አዲስ ነው የተወለደችው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ በአጭር ጊዜ የተገነቡ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች ከተማዋን አዘምነዋታል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው በመዲናዋ የሚኖሩ የውጭ ሀገራት ዜጎች ገለጹ።
አዲስ አበባ የህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ ርዕሰ ከተማ፣ የአፍሪካ መዲና፣ የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል እና የውጭ ዜጎችን ጨምሮ የብዙኃን መኖሪያና የጉብኝት ከተማ ናት።
ይህች ታሪካዊ ከተማ ለወትሮው በአየር ንብረቷ እንጂ በመሰረተ ልማት ዝርጋታዋ በበጎ አትጠቀስም ነበር።
ዛሬ ላይ ግን ያ ታሪክ ተቀይሯል። የለውጡ መንግሥት እንደ አዲስ መልሶ ከገነባቸው ታላላቅ ስኬቶች መካከል አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ እና ፅዱ ያደረጋት የኮሪደር ልማት ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይይዛል።
አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲናነቷን ይበልጥ ለማስቀጠልና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን በሁሉን አቀፍ የለውጥ ጎዳና ላይ ትገኛለች።
ዛሬ ከተማዋ ታሪካዊ ቅርሶቿን ጠብቃ፣ የነዋሪዎቿን የኑሮ ጥራት ባሻሻለ እና የውጭ ዜጎችን ቀልብ በሳበ መልኩ የዘመናዊነት ማማ እየሆነች ነው።
ይህ የመዲናዋ ፈጣን ለውጥ በብዙ የዓለም መሪዎችና በአፍሪካውያን ዘንድ ከፍተኛ አድናቆት እየተቸረው ይገኛል።
በተለይም በከተማዋ በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሰማርተው የሚኖሩ የውጭ ሀገራት ዜጎች የአዲስ አበባን ዕድገትና የዝማኔ ጉዞ በዓይናቸው እያዩት፣ በፈጣን ጊዜ ውስጥ የተሳካ መሆኑ እያስደነቃቸው ነው።
ለወትሮው ይመለከቷቸው የነበሩት ጎስቋላ ሰፈሮች፣ የተቆፋፈሩና ለእግረኛ የማይመቹ መንገዶች ዛሬ እጅግ ዘምነዋል። ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የከተማ መዝናኛ፣ መኖሪያና የሥራ ከባቢም ተፈጥሯል።
በአዲስ አበባ በሚኖሩትና በኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት በአይሲቲ የትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ህንዳዊው ፕሮፌሰር ራቪንድራ ባቡ፣ የከተማዋን ለውጥ ማመን ነው ያቃተኝ፤ ልክ እንደ አዲስ ነው የተወለደችው ሲሉ ነው የገለጹት።
አዲስ አበባን ከለውጥ በፊት፣ የለውጥ ሂደቱንና ከለውጥ በኋላ በአግባቡ እንደተመለከቷት ጠቅሰው፤ በፊት ከሚያውቋት ፍጹም በተለየ መልኩ ወደ ከፍተኛ የዕድገት ጎዳና ተሻግራ በማየታቸው መደነቃቸውን ይናገራሉ።
የከተማዋን ገጽታ የሚያስውቡና ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው የመሠረተ ልማት ሥራዎች በስፋት መገንባታቸው ለከተማዋ መዘመን ጉልህ አበርክቶ እንዳለው ነው ያነሱት ፕሮፌሰሩ።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ጸጋ የታደለች እና ምቹ የሆነ የአየር ጸባይ ያላት ሀገር መሆኗንም ይመሰክራሉ።
በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑትና በኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የኮንፊሽየስ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር የሆኑት ቻይናዊው ፓን ሊያንግ፤ የአዲስ አበባ ዕድገት ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ የዘመናዊነት ጉዞ ነው ይላሉ።
የከተማዋ የተቀናጀ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ሲከናወን በቅርበት መመልከታቸውን ጠቅሰው፤ የወንዝ ዳርቻና ሌሎች የልማት ሥራዎች ከተማዋ ውብ እንድትሆን እያደረጓት መሆኑን ይናገራሉ።
አዲስ አበባ በአጭር ዓመታት ያስመዘገበችው ስኬትም የአፍሪካ የዘመናዊነት መሠረትና የፈጣን ልማት ምሳሌ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአዲስ አበባን ገጽታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከቀየሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ሰፊ የእግረኛ መንገዶች፣ የብስክሌት መንገዶችን፣ አረንጓዴ ስፍራዎችንና ዘመናዊ የመንገድ መብራቶችን፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የመኖሪያና የንግድ ስፍራዎችን በማካተት መዲናዋን ወደ ዓለም አቀፍ የዝማኔ ደረጃ አሳድጓታል።
የወንዝ ዳርቻ ልማትም ቀደም ሲል በቆሻሻ የተበከሉ የወንዝ ዳርቻዎችን ወደ ውብ የሕዝብ መዝናኛነት የቀየረ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።
ፕሮፌሰር ራቪንድራ ባቡ እና ፓንሊያንግ እንደሚመሰክሩት የከተማዋ አየር ንብረትና መልክዓ-ምድር ተስማሚ በመሆኑ፣ ከኮሪደርና ከአረንጓዴ ልማት ጋር ተዳምሮ ለቱሪዝምና ለኑሮ እጅግ ተመራጭ አድርጓታል።