የመስኖ መሰረተ ልማት ውጤታማነት የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት የማረጋገጥ ስኬታማ ጉዞ እየገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመስኖ መሰረተ ልማት ውጤታማነት የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት የማረጋገጥ ስኬታማ ጉዞ እየገነባ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦የመስኖ መሰረተ ልማት ውጤታማነት በግብርና ዘርፍ የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት የማረጋገጥ ስኬታማ ጉዞ እየገነባ መሆኑን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ አብዱረህማን አብደላ ገለጹ።
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ከክልል መስኖ ቢሮ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በውስጥ ስታንዳርድ ዝግጅትና ትግበራ ዙሪያ የልምድ ልውውጥ መድረክ እያካሄደ ይገኛል።
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ አብዱረህማን አብደላ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የመስኖ ፕሮጀክቶችን በጥራትና ፍጥነት በማጠናቀቅ የልማት አቅም እንዲሆኑ እየተደረገ ነው።
የመስኖ መሰረተ ልማት ውጤታማነትን ለማሻሻልም በስታንዳርድ መምራት የሚያስችሉ በርካታ የአሰራር ሥርዓቶች ተዘጋጅተው ስራ ላይ እንዲውሉ መደረጉን ገልጸዋል።
የስታንዳርድ የአሰራር ሥርዓቶችም በፌደራልና የክልል መንግሥታት የሚከናወኑ የመስኖ ልማት ሥራዎችን በተደራጀ መልኩ እንዲመሩ በማስቻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ በተቀናጀ አግባብ የሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ሥራዎች የመስኖ ልማት ሽፋንን በማሳደግ በምርታማነት ዕድገት ላይ ወሳኝ ሚና እየተወጡ ነው ብለዋል።
በመስኖ መሰረተ ልማት ውጤታማነትም የበጋ መስኖ ስንዴን ጨምሮ በሁሉም ዘርፍ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ አስደናቂ ውጤት እየተገኘ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ስኬታማ ጉዞን እያፋጠነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን የግብርና ልማት ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ በሁሉም ወቅቶች የማምረት ስራ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።