ቀጥታ፡

ምርጫው ሕዝባችን ለሰላም ሲባል ውድ ዋጋ ከፍሎ ያሸነፈበት ወሳኝ የታሪክ እጥፋት ነው-አብን

አዲስ አበባ፤ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፡-7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝባችን ለሰላም ሲባል ውድ ዋጋ ከፍሎ ያሸነፈበት ወሳኝ የታሪክ እጥፋት ነው ሲል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ገለጸ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ትናንት ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።

ይህን ተከትሎም የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫውን ሂደት ስኬታማነት በመግለጽ፤ ውጤቱን በጸጋ መቀበላቸውን እና በአብላጫ ድምጽ ላሸነፈው ብልጽግና ፓርቲም የመልካም ምኞት መግለጫ እያስተላለፉ ነው።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በበኩሉ ባወጣው መግለጫም፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝባችን ለሰላም ሲባል ውድ ዋጋ ከፍሎ ያሸነፈበት ወሳኝ የታሪክ እጥፋት ነው ብሏል።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝቡ ወደ ተሻለ የፖለቲካ እና የማኅበረ-ኢኮኖሚ ምዕራፍ ለመሻገር ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበት ውሳኔ መሆኑንም አመላክቷል።

የተመዘገበው ስኬት የማህበረሰባችን የአርቆ አሳቢነት ትሩፋት በመሆኑ ወሳኝ የታሪክ እጥፋት ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባም ነው ብሏል በመግለጫው፡፡

ምርጫው ሕዝባችን ፈተናዎችን ተቋቁሞ በታሪክ የሚዘከር የአይበገሬነት ታሪክ የጻፈበት፣ ለዘላቂ ሰላምና እድገት የሚበጅ የፖለቲካ ባህል አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ ያደረገበት፣ በዋናነት የማኅበረ-ፖለቲካ ግብረ-ገብ እሴቶች ተቃራኒ የሆኑ ጯሂና እኩይ ድምጸቶችን ማሸነፍ የቻለበት፣ ለሰላም ሲባል ዋጋ የመክፈል ቁርጠኝነት የታየበትና ዋጋ የተከፈለበት መሆኑንም ነው የገለጸው።

ሕዝብን ማሸነፍ አይቻልምና ድሉ የሰላም ወዳዱ ሕዝብ ሆኗልም ነው ያለው።

ምርጫው ለውጫዊ የኢትዮጵያ ጠላቶችም ተስፋ ያስቆረጠ ክስተት መሆኑንም አብን ገልጿል።

ዳያስፖራው ልማቶችንና የሰላም እንቅስቃሴዎችን እንዲደግፍ እንዲሁም ለሀገራዊ መረጋጋት ፋይዳ ከሌላቸው አጀንዳዎች ራሱን እንዲያርቅ አብን ጥሪ አቅርቧል።

በመጨረሻም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አብላጫ ድምጽ ላገኘው ብልጽግና ፓርቲ የእንኳን ደስ አላችሁ መልካም ምኞቱን ገልጾ፤መጭው ጊዜ ሀገራችንን ወደ ተሻለ ሁለንተናዊ ምዕራፍ የምናሻግርበት ነው ሲል ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም