ዩኒቨርሲቲው የቱሪዝም ዘርፉን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያግዙ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ያጠናክራል - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው የቱሪዝም ዘርፉን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያግዙ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ያጠናክራል
ሮቤ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦ የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም ዘርፉን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያግዙ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እንደሚያጠናክር ገለጸ።
ዩኒቨርሲቲው "የቱሪዝምና መስተንግዶ ትምህርትን በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ማዕቀፍ መቃኘት" በሚል መሪ ሐሳብ 2ኛውን ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ኮንፈረንስ ማካሄድ ጀምሯል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እና የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፤ በኮንፈረንሱ መክፈቻ ላይ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፉን በማልማት ዓለም አቀፍ ተመራጭነቷን ለማስፋት በምታደርገው ጥረት ቴክኖሎጂ ዋና ግብዓት ነው ብለዋል።
በዚህም የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ከዲጂታል 2030 ስትራቴጂ ጋር በማስተሳሰር ወደ ሥራ መገባቱንም አንስተዋል።
ይህም በቱሪዝም ዘርፉ የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል ልማት በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የራሱ ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል።
መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የባሌና አካባቢውን የቱሪዝም እምቅ አቅም ለማልማት የሚደረገውን ጥረት በምርምርና በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እንዲደገፍ ለማድረግ መሥራቱ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
የአሁኑ የምርምር ኮንፈረንስ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የቱሪዝም ልማት ኢኒሼቲቭ ለማሳካት መሠረት እንደሚጥል ተናግረዋል።
ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈው ይህ የምርምር መድረክ፤ ዩኒቨርሲቲው በቱሪዝም ዘርፍ የጀመረውን የማስተዋወቅ፤ የማነቃቃትና የምርምር ሥራዎች ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ተጨማሪ አቅም እንደሚሆንም አክለዋል።
የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሃነመስቀል ጠና (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን የቱሪዝም እምቅ አቅም ለማልማት የሚደረገውን ጥረት በምርምር እያገዘ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለዚህም በባሌና በምሥራቅ ባሌ አካባቢ የሚገኙ በርካታ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ የቱሪስት መስህቦችን በሳይንሳዊ መንገድ የማጥናት፤ የማስተዋወቅና እንዲለሙ በቅንጅት የመሥራት ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ለአብነትም የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክና የድሬ ሼህ ሁሴን የመስህብ ስፍራዎች እንዲለሙና እንዲተዋወቁ ዩኒቨርሲቲው የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አመልክተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ያዘጋጀው ይህ ዓለም አቀፍ የምርምር ኮንፈረንስም የቱሪስት መስህቦችን ለማልማትና ለማስተዋወቅ እያደረገ ላለው ጥረት አንዱ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው፤ የቱሪዝም ዘርፉን ተወዳዳሪ ለማድረግ በቱሪስት መዳረሻዎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ለዚህም የሰው ኃይል ልማትን ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር ባለሙያዎች በዕውቀትና በክህሎት ብቁ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለተግባራዊነቱም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የቱሪዝምና የሆቴል ኢንዱስትሪውን የሚመጥን ብቁ ባለሙያ የማፍራት ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው፤ የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ እያደረጋቸው ያሉ የምርምር ሥራዎች ለዚህ ጥረት ትልቅ አጋዥ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከኮንፈረንሱ መክፈቻ ጎን ለጎንም መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከዩናይትድ ኪንግደም (UK) የመጡ የባለሙያዎች ቡድን ጋር በቅርብ ትብብር ያበለጸገውንና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀውን አዲሱን የዩኒቨርሲቲውን ድረ-ገጽ በይፋ አስመርቋል።