ቀጥታ፡

ብልጽግና ፓርቲ ህዝብ የሰጠውን ኃላፊነት በመወጣት የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ማስቀጠል ይጠበቅበታል

አሶሳ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦ ብልጽግና ፓርቲ ሕዝብ የሰጠውን አደራና ኃላፊነት በመወጣት፣ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትናንት ባስታወቀው መሠረት ብልጽግና ፓርቲ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አብላጫ የምክር ቤት መቀመጫዎችን በማግኘት አሸንፏል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች፤ አሸናፊው ብልጽግና ፓርቲ ተጨማሪ የህዝብ አደራን በመቀበል ለቀጣይ አምስት ዓመታት መሠረታዊ የልማት ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችለውን ዕድል አግኝቷል።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አልሃጂ ሀሊፋ እንደተናገሩት፤ የምርጫው ውጤት ብልጽግና ፓርቲ እያከናወናቸው የሚገኙ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ የተሻለች ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ሂደት አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል።

ፓርቲው የህዝቡን ይሁንታ ያገኘ በመሆኑ ከህዝቡ የሚነሱ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና ሰላም የማስከበር ጥያቄዎችን ለመመለስ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆን እንዳለበትም ገልጸዋል።

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ጉዴታ ነጋሳ በበኩላቸው፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሁሉም መስክ ስኬታማ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም በህዝብ ተወካዮች እና በክልል ምክርቤቶች ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ከዚህ በፊት ከነበረው የተሻለ መቀመጫ ማግኘታቸው የፖለቲካ ምህዳሩ እየሰፋ መምጣቱን ያሳያል ብለዋል።

አሸናፊው ብልጽግና ፓርቲም ያገኘውን ዕድል በመጠቀም በሁሉም አካባቢዎች አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን እና የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ትልቅ የቤት ስራ እንደሚጠብቀው ተናግረዋል።

የምርጫው ውጤት የኢትዮጵያን አሸናፊነት ያረጋገጠ እና የህዝብ ድምጽ ምን ያክል ዋጋ እንዳለው ያስመሰከረበት ነው ያሉት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ አቶ አደም ሳለህ ናቸው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ሂደቱን ነፃ እና ገለልተኛ ሆኖ ያከናወነበት ሁኔታ የሚደነቅ መሆኑን በመጥቀስ።

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሕዝብ ተወካዮች እና ለክልል ምክር ቤቶች ብልጽግና ፓርቲ አብላጫ የምክር ቤት መቀመጫ በማግኘት ማሸነፉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትናንት ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

የምርጫው ውጤት ይፋ መደረጉን ተከትሎም ብልጽግና ፓርቲ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ምስጋና ያቀረበ ሲሆን፤ ፓርቲው በቅድመ ምርጫ ለህዝብ የገባውን ቃል ሳይሸራረፍ በመተግበር ሕዝብን በቅንነትና በታማኝነት እንደሚያገለግልም አረጋግጧል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም