ቀጥታ፡

የክልሉን የገቢ አቅም በማሳደግ የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዶችን ለማሳካት ትኩረት ተሰጥቷል

ጋምቤላ  ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል የገቢ አቅምን በማሳደግ የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዶችን ለማሳካት ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ።

በክልሉ የገቢ እቅድ አተገባበር ዙሪያ የገቢ ሰብሳቢ ተቋማት አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።


 

የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ኡማን አሙሉ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ ክልሉ የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ የታለሙትን የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዶች ለማሳካት ትኩረት ተሰጥቷል።

ለእቅዱ ስኬታማነት የዘርፉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ቁርጠኝነት የላቀ ድርሻ ያለው መሆኑን አስገንዝበዋል።

የግብር አሰባሰብ ሂደቱ ፍትሃዊ፣ ግልጽና ዘመናዊ አሰራርን የተከተለ እንዲሆን በትጋት እንደሚሰራ አመላክተዋል።


 

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ቸንኮት ዴቪድ በበኩላቸው፤ በክልሉ ያለውን የገቢ አቅም በአግባቡ ለመሰብሰብና ለመጠቀም አዳዲስ አሰራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

የውይይት መድረኩ ዋና ዓላማም በአዳዲስ አሰራሮች ላይ የሚመለከታቸው አካላት በቂ ግንዛቤ ይዘው እንዲሰሩ ማስቻል መሆኑን አስታውቀዋል።

በክልሉ ባለፉት 11 ወራት ከ4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም