የሰው ሰራሽ አስተውሎትና ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም አስተማማኝ የሃይል አቅርቦት እንዲፈጠር እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሰው ሰራሽ አስተውሎትና ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም አስተማማኝ የሃይል አቅርቦት እንዲፈጠር እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦የሰው ሰራሽ አስተውሎትና ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም አስተማማኝ የሃይል አቅርቦት እንዲፈጠር እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪከ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ጌቱ ገረመው ገለጹ፡፡
ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው ለኢዜአ እንዳሉት፤ አገልግሎቱ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት መስመሮችንና የዲስትሪቡዩሽን ትራንስፎርመሮችን ብቃት ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ ነው።
የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ችግርን ለመፍታት የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማትን የማሻሻል፣ መልሶ የማቋቋምና የቅድመ-መከላከል ጥገና ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ድንገተኛ ብልሽቶችን አስቀድሞ ለመለየትና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ለመዘርጋትም ዘመናዊ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችንና የሰው ሰራሽ አስተውሎት ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪከ አገልግሎት፣ ከመንግሥትና የልማት አጋሮች የሚመነጭ የገንዘብ ሃብትን በመጠቀም መሰረተ ልማት የማሻሻል ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ከመሠረተ ልማት ግንባታው ጎን ለጎንም የደንበኞችን አገልግሎት ጥራትና ፍጥነት ማሻሻል የሚያስችሉ ሰፋፊ የትራንስፎርሜሽን ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
አዳዲስ አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን በመተግበር የኔትወርክ አቅምን የማሳደግ፣ መልሶ የማደራጀትና የቅድመ-መከላከል ጥገና ሥራዎች በቅንጅት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
ደንበኞች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻልም የውስጥ አቅምን የማጠናከርና የጥገና ቡድኖችን በአዲስ መልክ የማደራጀት ሥራ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የተፈጠረው ውጤታማ የደንበኞች አገልግሎትም ውጤታማነትን እያሻሻለ መሆኑን አስረድተዋል።