ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማስፋፋት ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ዕድገት አርዓያ የሚሆን ስኬት እያስመዘገበች ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማስፋፋት ለታዳሽ ኃይል አጠቃቀምና ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ዕድገት አርዓያ የሚሆን ስኬት እያስመዘገበች መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትን በሚያሳልጡ የትራንስፖርት፣ ኢንዱስትሪ፣ ኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎች እና በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ በትኩረት እየሰራች ነው፡፡

በዚህም በየዓመቱ ለነዳጅ የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስና በታዳሽ ኃይል የሚመራ የትራንስፖርት ሥርዓት በከፍተኛ ሁኔታ በመገንባት ላይ ትገኛለች፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ከአስራ ስምንት በላይ የፌደራል ተቋማት የተሳተፉበትን አዲስ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ስትራቴጂ (2025-2030) እና የትግበራ እቅድ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ 

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ስትራቴጂው የሀገሪቱን የትራንስፖርት ዘርፍ ወደ ኤሌክትሪክ ሃይል የመቀየር ሂደትን በፈጣን ሁኔታ ወደ ተግባር ለማስገባት እና የተቋማትን ቅንጅት ለማጠናከር ታስቦ የተዘጋጀ ነው። 


 

ኢትዮጵያ የነዳጅ ወጪን ለመቀነስ እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ተደራሽነት ለማስፋፋት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ እና የታክስ ማበረታቻ ፖሊሲዎችን በማውጣት ረገድ ትልቅ ስራ እያከናወነች ትገኛለች ብለዋል።

መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ የተለያዩ ማበረታቻዎች መደረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም መሰረት ሙሉ በሙሉ ተገጣጥመው ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚጣለው የጉምሩክ ቀረጥ ትልቁ እስከ ሰላሳ አምስት በመቶ እንዲሆን መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ይህ ቀረጥ አጠቃላይ የኤክሳይዝ፣ የሱር እና የተጨማሪ እሴት ታክስን ያካተተ በመሆኑ አስመጪዎችን በእጅጉ ያበረታታ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በሀገር ውስጥ የሚገጣጠሙ ተሽከርካሪዎች ከጉምሩክ ቀረጥ ነፃ መደረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ የኤሌክትሪፊኬሽን እቅድ በቤት አውቶሞቢሎችና በህዝብ ትራንስፖርት ብቻ ሳይወሰን፣ ድንበር ተሻጋሪ ትራንስፖርትና ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎችንም ያካተተ እንዲሆን መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሰረት በሀገር ውስጥ እስከ 20 ቶን የሚመዝኑ የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎችን የመገጣጠም ሥራ መጀመሩን ጠቅሰው፤ በትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይም በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ከባድ ማሽነሪዎች መሰማራት መጀመራቸውን አክለዋል፡፡


 

በሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ከ145 ሺህ በላይ መድረሱን አመልክተው፤ በአሁኑ ወቅት በዘጠኝ ከተሞች የኤሌክትሪክ አውቶቡስ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታውቀዋል።

የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ከማስፋፋት አኳያ፣ የኮሪደር ልማት የሚገነቡ ከተሞች የተሽከርካሪ ቻርጅ መሙያ ጣቢያዎችን እየገነቡ መሆኑን አክለው፤ በአዲስ አበባ ከተማ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ውስጥ 1 ሺህ 176 ፈጣን የቻርጅ መሙያ ጣቢያዎችን ለማሟላት ዕቅድ መያዙንም ጠቁመዋል፡፡

ጣቢያዎችን ለማሟላትም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ከኢትዮ ቴሌኮም እና ከሌሎች ባለድርሻ ተቋማት ጋር በመቀናጀት አዲስ ሀገራዊ መመሪያ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል፡፡

ከመሠረተ ልማት ዝርጋታው በተጓዳኝ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን የባትሪ ጥገና፣ መልሶ መጠቀም እና የባትሪ ምርት ላይ ትኩረት በማድረግ፣ ከቴክኖሎጂና ምርምር ተቋማት ጋር የጋራ የሳይንሳዊ ምርምር ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ይህ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ንቅናቄ የሀገሪቱን የነዳጅ ጥገኝነት በመቀነስ፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥና የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ በዘላቂነት ለማሻሻል ትልቅ አቅም የሚገነባ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም