ቀጥታ፡

መንግስት ከሚመሰርተው ፓርቲ ጋር ተባብረን በመስራት ለሀገር እድገትና ብልጽግና የበኩላችንን እንወጣለን

ባህር ዳር/ደብረ ብርሃን፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦በጠቅላላ ምርጫው አብላጫ የምክር ቤት መቀመጫ በማግኘት አሸናፊ ከሆነው ብልጽግና ፓርቲ ጋር ተባብረን በመስራት ለሀገር እድገትና ብልጽግና የበኩላችንን እንወጣለን ሲሉ የባህር ዳር እና የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተወዳደሩበት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ህዝቡ ድምጹን በነጻነት በመስጠት መንግስት ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በምርጫ ብቻ መመስረት እንዳለበት ያለውን ጽኑ ፍላጎቱን አሳይቷል። 

በዚሁ መሰረት በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ መንግስት ለመመስረት የሚያስችለውን አብላጫ የምክር ቤት መቀመጫ ማግኘቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትናንት ይፋ አድርጓል።

በምርጫው ውጤት ላይ ኢዜአ በባህር ዳር እና በደብረ ብርሃን ከተማ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች፤ በጠቅላላ ምርጫው አብላጫ መቀመጫ ያገኘው ብልጽግና ፓርቲ በቀጣይ ለህዝብ ዘላቂ ሰላምና ልማት አበክሮ ይሰራል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ከምርጫው በፊት ለህዝብ ቃል በገባው መሰረት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮችን ለይቶ መስራት እንዳለበትም ተናግረዋል።

ነዋሪዎቹ ከፓርቲው ጋር ተባብረው በመስራት በሀገር እድገትና ብልጽግና ላይ የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ነው ያረጋገጡት።

የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ አቶ በትግሉ ተስፋሁን እንዳሉት፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ያስቻለ እንቅስቃሴ በተግባር ተስተውሏል።

በምርጫው አብላጫ የምክር ቤት መቀመጫ በማግኘት አሸናፊ የሆነው ብልጽግና ፓርቲ መንግስት ሲመሰርት ከምርጫ በፊት በገባው ቃል መሰረት ሰላምን ማጽናት እንዳለበት ገልጸዋል።

እንዲሁም የህዝብን የላቀ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማት ሥራዎችን በማፋጠን የህዝብ አለኝታነቱን ዳግም ማረጋገጥ አለበት ብለዋል።

በተመሳሳይ የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎችም በምርጫው ካሸነፈው ብልጽግና ፓርቲ ጋር ተባብረው በመስራት በሀገር እድገትና ብልጽግና ላይ የራሳቸውን አሻራ እንደሚያሳርፉ አረጋግጠዋል። 

ከከተማው ነዋሪዎች መካከል የአፄ ዘርዓያዕቆብ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ሀብታሙ ሞገስ እንዳሉት፣ በጠቅላላ ምርጫው አብላጫ ድምጽ ያገኘው ብልጽግና ፓርቲ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማትን ማረጋገጥ ላይ አተኩሮ መስራት አለበት።

ለምርጫው ያደረጉትን ንቁ ተሳትፎ በቀጣይም ከፓርቲው ጋር በልማት በመተባበር ለሀገር እድገት የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።

በእቴጌ ጣይቱ ክፍለ ከተማ ጊዮርጊስ ቀበሌ ነዋሪ መቶ አለቃ ሰለሞን ዘለቀ በበኩላቸው እንዳሉት፤  በህዝብ የተመረጠው ብልጽግና ፓርቲ የተጀመሩ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ዳር ለማድረስ መትጋት አለበት።

እርሳቸውም የሚመሰረተው መንግስት የሀገርን ሰላም በዘላቂነት በማረጋገጥ የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሚናቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

የጠባሴ ክፍለ ከተማ መሳለሚያ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት እጅጋየሁ ሽፈራው በበኩሏ እንዳለችው፤ በህዝብ ድምጽ የተመረጠው ብልጽግና ፓርቲ ወጣቱን በሥራ ዕድልና በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ የገባውን ቃል በተግባር ማሳየት አለበት።

እንደ ወጣትነቷ ባላት እውቀትና ልምድ በፈጠራና በቴክኖሎጂ ላይ አተኩራ በመስራት በሀገር የብልጽግና ጉዞ ላይ አሻራዋን ለማሳረፍ ቁርጠኛ መሆኗን ተናግራለች።

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሕዝብ ተወካዮች እና ለክልል ምክር ቤቶች ብልጽግና ፓርቲ አብላጫ የምክር ቤት መቀመጫ በማግኘት ማሸነፉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትናንት ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

የምርጫው ውጤት ይፋ መደረጉን ተከትሎም ብልጽግና ፓርቲ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ምስጋና ያቀረበ ሲሆን፤ ፓርቲው በቅድመ ምርጫ ለህዝብ የገባውን ቃል ሳይሸራረፍ በመተግበር ሕዝብን በቅንነትና በታማኝነት እንደሚያገለግልም አረጋግጧል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም