ቀጥታ፡

የተጀመሩ የልማት ስራዎች እንዲፋጠኑ የምናደርገውን ተሳትፎ አጠናክረን እንቀጥላለን-ወጣቶች

አምቦ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦ከአሸናፊው ፓርቲ ጎን በመቆም የአካባቢያችንን ሰላም በመጠበቅ የተጀመሩ የልማት ስራዎች እንዲፋጠኑ የምናደርገውን ተሳትፎ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የአምቦ ከተማ ወጣቶች ገለጹ።

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሕዝብ ተወካዮች እና ለክልል ምክር ቤቶች ብልጽግና ፓርቲ አብላጫውን መቀመጫ በማግኘት ማሸነፉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአምቦ ከተማ ወጣቶች፤ የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ የተጀመሩ የልማት ስራዎች እንዲፋጠኑ ከአሸናፊው ፓርቲ ጎን በመሆን የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወጣት ሽብሩ ነገሪ፤ ብልጽግና ፓርቲ የሕዝቡን ጥያቄ መፍታት የሚችሉና ቀደም ሲል በሀገርና በክልል ደረጃ የተጀመሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል አለበት ብሏል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የታቀዱ ግዙፍ የልማት ስራዎች እንዲሳኩ ከፓርቲው ጎን በመሆን የበኩሉን እንደሚወጣ ገልጿል።

በከተማዋ በሁሉም ዘርፎች እየተካሄዱ ያሉ የልማት ሥራዎችን ለማገዝ መዘጋጀቱን የገለጸው ደግሞ ወጣት ዮሐንስ ሚደቅሳ ነው። 

ከአሸናፊው ፓርቲ ጋር በመሆን በተጀመሩ የልማት ሥራዎች ላይ በመሳተፍ እንዲሁም የአካባቢውን ወጣቶች በማስተባበር የሚጠበቅበትን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

ወጣት ጭምዴሳ ነገሪ በበኩሉ፤ አብላጫ የምክርቤት መቀመጫ ያገኘው ፓርቲ ከዚህ ቀደም ዜጎች ሲያነሷቸው የነበሩ የልማት ጥያቄዎችን መመለስ ይጠበቅበታል ብሏል።

የተጀመሩና የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲቀጥሉ የበኩሉን እንደሚወጣም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም