ቀጥታ፡

የዓለም ዋንጫ ሁለተኛ ዙር ጨዋታ፤ ሴኔጋል ከኖርዌይ፡አልጄሪያ ከጆርዳን

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የምድብ 9 እና 10 ሁለተኛ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።

በምድብ ዘጠኝ ኖርዌይ ከሴኔጋል በኒው ዮርክ ኒው ጀርዚ ስታዲየም ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ ኖርዌይ ኢራቅን 3 ለ 1 ስትረታ ሴኔጋል በፈረንሳይ 3 ለ 1 ተሸንፋለች።

ኖርዌይ ካሸነፈች ጥሎ ማለፍ መግባቷን ታረጋግጣለች።

የምዕራብ አፍሪካዋ ሴኔጋል ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ህልሟን እውን ለማድረግ ከጨዋታው ሶስት ነጥብ ማግኘት ይጠበቅባታል።

በዚሁ ምድብ ፈረንሳይ ከኢራቅ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ላይ በፊላደልፊያ ስታዲየም ይጫወታሉ።

የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት ያገኘችው ፈረንሳይ ድል ከቀናት ወደ ጥሎ ማለፉ ትገባለች።

ኢራቅ በውድድሩ ላይ ለመቆየት ከጠንካራዋ ፈረንሳይ ሶስት ነጥብ ማግኘት ይጠበቅባታል።

በምድብ 10 ጆርዳን ከአልጄሪያ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ላይ በሳንፍራንሲስኮ ቤይ ኤሪያ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

በመጀመሪያው የምድብ ጨዋታቸው ጆርዳን በኦስትሪያ 3 ለ 1፣ አልጄሪያ በአርጀንቲና የ3 ለ 0 ሽንፈት አስተናግደዋል። 

ሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ድላቸውን ለማስመዝገብ ይፋለማሉ። አሸናፊው ቡድን ወደ ጥሎ ማለፍ የመግባት ተስፋውን ያለመልማል።

በዚሁ ምድብ አርጀንቲና ከኦስትሪያ ምሽት ሁለት ሰዓት ላይ በዳላስ ስታዲየም ይጫወታሉ።

የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸውን ያሸነፉት ሁለት ሀገራት የሚያደርጉት ጨዋታ ትኩረትን ስቧል።

ጨዋታውን የሚያሸንፈው ሀገር ወደ ጥሎ ማለፍ መግባቱን ያረጋግጣል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም