ቀጥታ፡

በነቀምቴ ከተማ ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ተዘጋጅተዋል

ነቀምቴ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦በነቀምቴ ከተማ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መዘጋጀታቸውን የከተማው ግብርና ፅህፈት ቤት ገለጸ።

የነቀምቴ ከተማ ግብርና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ ከድር፤ በከተማዋ ዘንድሮ ለምግብነት፣ ለአፈር ለምነት፣ ለከተማ ውበትና ለደን ልማት የሚውሉ 790 ሺህ ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።


 

በከተማው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተጀመረ ወዲህ በተተከሉ ችግኞች ከፍተኛ ለውጥ መመዝገቡን ኃላፊው ገልጸዋል። 

በዚህም የተራቆቱ መሬቶችን በዕፅዋት ለመሸፈን፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንዲሁም የኅብረተሰቡን ችግኝ የመትከልና የመንከባከብ ባህል ለማጠናከር ተችሏል ብለዋል።

የታቀደውን ግብ ለማሳካትም በግል፣ በመንግሥት እንዲሁም በጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራት በሚንቀሳቀሱ 13 የችግኝ ጣቢያዎች ውስጥ ችግኞቹ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የዘንድሮው የችግኝ ተከላ በ15 ሄክታር መሬት ላይ የሚከናወን ሲሆን፣ በዚሁ መሬት ላይ ከ700 ሺህ በላይ የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቁመዋል። 

በከተማዋ 65 ሺህ ነዋሪዎች በችግኝ ተከላው ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም ተከላው በይፋ መጀመሩን አንስተዋል። 

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ የአየር ንብረት ሚዛንን ከመጠበቅ ባለፈ፣ እስካሁን ከ150 ሺህ በላይ ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረጉንም ኃላፊው ጠቅሰዋል።

የከተማዋ የጨለለቂ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አበበ ኢድሪስ፣ ለአመታት በችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ  ሲሳተፉ መቆየታቸውን ገልጸዋል። 


 

ከራሳቸው አልፈው ልጆቻቸው ዛፍ የመትከል ባህል እንዲያዳብሩና የተተከሉትን እንዲንከባከቡ የበኩላቸውን ኃላፊነት እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል። 

የበኬጀማ ቀበሌ ነዋሪ አቶ እውነቱ ኃይለየሱስ በበኩላቸው፣ በየዓመቱ በችግኝ ተከላው ላይ አሻራቸውን በማኖር ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።


 

በተለይም ችግኝ መትከል ብቻ በቂ እንዳልሆነ የገለጹት አቶ እውነቱ፣ የመንከባከብ ሥራም በዚያው ልክ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ በመሆኑ በከተማዋ ተጨባጭ ለውጥ እየታየ ነው ብለዋል። 

በዚህም ዝናብ ጊዜውን ጠብቆ እንዲዘንብ፣ ወንዞችና የደረቁ ኩሬዎች እንዲሞሉ እንዲሁም አካባቢው ከቀድሞው ይበልጥ ለምና አረንጓዴ እንዲላበስ ማገዙን ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም