ቀጥታ፡

አሸናፊ ሆኖ ለተመረጠው ብልጽግና ፓርቲና በምርጫው ለተሳተፋችሁ ሁሉ እንኳን ደስ ያላችሁ -ኢዜማ

አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦ መሪ ሆኖ እንዲቀጥል ለተመረጠው ብልጽግና ፓርቲ እንዲሁም በውድድሩ ተሳትፋችሁ የሕዝብ ውክልናን ላሳካችሁ ተፎካካሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ ሲል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ(ኢዜአ) ገለጸ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትላንትናው መግለጫው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ በአብዛኛው የምርጫ ክልሎች አሸናፊ መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል።

ይሄንን ተከትሎ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ(ኢዜማ) ዛሬ ባስተላለፈው መልዕክት ፓርቲው በተወዳደረባቸው ቦታዎች 13 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና 73 የክልል እና የከተማ ምክር ቤት ወንበሮችን በማግኘቱ ለአባሎቹ እና ለደጋፊዎቹ እንኳን ደስ ያላችሁ ብሏል።

በዘንድሮው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ባገኘው ውጤትም በሃገር አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ ፓርቲ ሆኖ ማጠናቀቁን ገልጿል።

ስኬቱን ያስመዘገቡ የፓርቲውን ዕጩዎች፣ አባላትና ደጋፊዎችን ያመሰገነው ፓርቲው ከቀጣዩ ምርጫ በፊት ባሉት ዓመታት ጠንካራ ጎኖቹን በማስቀጠል ክፍተቶቹን በስትራቴጂ እና ሌሎች አስፈላጊ ተግባራት በመሙላት ተጨባጭ የተፎካካሪ ፓርቲነት ሚናውን ጊዜ ሳያባክን የሚጀምረው ዛሬ መሆኑንም ገልጿል።

በነዚህ ዓመታት ቀደም ሲል ስናደርገው እንደነበረ ሁሉ ብሔራዊ ጥቅሞችን በሚያሣኩ ጉዳዮች ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃይል ጋር በመተባበር የምንንቀሳቀስበት ይሆናል ብሏል።

መፎካከሪያ አጀንዳዎች ላይ ማኅበረሰባችንን በሚመጥን ጨዋነት ልዩነቶቻችንንና ትችቶቻችንን እያቀረብን የጀመርነውን ጤናማና ዘመናዊ የፖለቲካ ባሕል የማዋለድ ተግባራችንን በተጠናከረ መልኩ የምንቀጥልበት እንዲሁም ለተጨማሪ ስኬት የምንንደረደርበት እንደሚሆን ቃል እንገባለን ሲልም ገልጿል።

ገዢ ሆኖ እንዲቀጥል ለተመረጠው ብልጽግና ፓርቲ እንዲሁም በውድድሩ ተሳትፋችሁ የሕዝብ ውክልናን ላሳካችሁ ተፎካካሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እንወዳለን ብሏል ፓርቲው በመልዕክቱ።

አሸናፊው ፓርቲ ከዛሬ ጀምሮ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ለመገንባትና ፍትሐዊ የፖለቲካ ምህዳርን ለሁሉም እኩል ተደራሽ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንዲሠራ፤ ለሀገር እድገትና ለውጥ ጠቃሚ ሀሳቦች ከማንኛውም ወገን ሊገኙ እንደሚችሉ በመረዳት አማራጭ ሃሳቦችን እንዲሰማ ጠይቋል።

እንዲሁም ትችቶችን በሆደ ሰፊነት እያስተናገደ ሀገራችን የሚያስፈልጋትን ዴሞክራሲ በጋራ እንድንገነባ ጥሪ እናቀርባለን ሲልም ኢዜማ ባስተላለፈው መልዕክት ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም