ቀጥታ፡

ብልጽግና ፓርቲ ብሔራዊ ጥቅምን በማስከበርና በዲፕሎማሲ ያመጣውን እመርታ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

አርባ ምንጭ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦ብልጽግና ፓርቲ ብሔራዊ ጥቅምን በማስከበር፣ በዲፕሎማሲ፣ በልማትና በዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ ያመጣውን እመርታ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሕዝብ ተወካዮች እና ለክልል ምክር ቤቶች ብልጽግና ፓርቲ አብላጫውን መቀመጫ በማግኘት ማሸነፉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

ቦርዱ ውጤቱን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች፤ ብልጽግና ፓርቲ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ሀገር የመምራት እድል ማግኘቱ የኢትዮጵያን እድገትና ማንሰራራት ለማስቀጠል ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል መምህር መስፍን ብርሃኑ እና ወይዘሮ ስሜነሽ መለሰ፤ በብልጽግና ፓርቲ መሪነት ባለፉት ዓመታት የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በማስከበር፣ በዲፕሎማሲ፣ በልማትና በዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ስኬታማ መሆኑን አንስተዋል።

በሀገሪቱ የተገነቡና አሁንም በግንባታ ላይ የሚገኙ ሜጋ ፕሮጀክቶችም የፓርቲው የስኬት መገለጫዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ፓርቲው በቀጣይ አምስት ዓመታት በተለይም ብሔራዊ ጥቅምን በማስከበር፣ በዲፕሎማሲ፣ በልማትና በዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ያመጣውን እመርታ አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የከተማዋ ነዋሪ አቶ ተስፋለም ባቤና፤ ብልጽግና ፓርቲ ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም ከመስራት ባሻገር በገበታ ለሀገርና ለትውልድ፣ በኮሪደር ልማት፣ በዲጂታል ልማትና ሌሎችም ተጨባጭ እድገት ማምጣቱን ተናግረዋል።

በመሆኑም እነዚህን መልካም ጅምሮች አጠናክሮ በመቀጠል ለሀገር እድገትና ለዜጎች ተጠቃሚነት ይበልጥ መስራት እንዳለበት አንስተዋል።

የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመጨረሻ ውጤት ይፋ መሆኑን ተከትሎ አሸናፊ የሆነው ብልፅግና ፓርቲ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ምስጋና አቅርቧል።

በመልዕክቱም በአጠቃላይ ብልፅግና ፓርቲ የገባውን ቃል ሳይሸራረፍ በመተግበር፣ ምርጫ የሥልጣን መቆናጠጫ ሳይሆን ሕዝብን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገያ ታላቅ አደራ መሆኑን ገልጿል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና በተግባር የማረጋገጥ ታሪካዊ ጉዟችንን ከምንጊዜውም በላይ በበለጠ ትጋት፣ አንድነትና ቁርጠኝነት አጠናክረን ለመቀጠል ለተከበረው ሕዝባችን ዳግም ቃላችንን እናድሳለን ሲል አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም