ቀጥታ፡

ከብልጽግና ፓርቲ ጋር በሁሉም የልማት ዘርፎች በትብብር ለመስራት ተዘጋጅተናል

ሀዋሳ ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦ አብላጫ ድምጽ በማግኘት መንግስት ከሚመሰርተው ብልጽግና ፓርቲ ጋር በሁሉም የልማት ዘርፎች በትብብር ለመስራት ተዘጋጅተናል ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ብልጽግና ፓርቲ አብላጫ የምክር ቤት መቀመጫ በማግኘት ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ሀገሪቱን የሚመራበትን ዕድል ማግኘቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

ኢዜአ በሀዋሳ ከተማ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደገለፁት፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰጠነው ድምጽ አሸናፊ ከሆነው ብልጽግና ፓርቲ ጋር በሁሉም የልማት መስኮች በጋራ እንሰራለን።

የሀዋሳ ከተማ ነዋሪው አቶ መስፍን ታሪኩ፤ በጠቅላላ ምርጫው ይመራናል፤ ያስተዳድረናል፤ ላልነው ፓርቲ ድምጻችንን ሰጥተናል ብለዋል።

በሰጠነው ድምጽ መሰረት አብላጫ ድምጽ በማግኘት መንግስት ከሚመሰርተው ብልጽግና ፓርቲ ጋር በሁሉም የልማት ዘርፎች በትብብር ለመስራት ተዘጋጅተናል ብለዋል።

ፓርቲው ኢትዮጵያ በሁለንተናዊ መልኩ የተሻለ ደረጃ ላይ እንድትገኝ የጀመረውን ተግባር በትኩረት እንዲያስቀጥልና የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች እንዲጠናከሩ ጠይቀዋል።

አቶ ሚካኤል ቢቸና በበኩላቸው፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሌት ብርድ የቀን ሀሩር ሳይበግራቸው ይመራናል ይበጀናል ያሉትን ፓርቲ መምረጣቸውን አስታውሰዋል።

የመረጥኩት ፓርቲ በማሸነፉ ደስተኛ ነኝ ያሉት አቶ ሚካኤል በቀጣይ መንግስት በመመስረት የሚያከናውናቸው የልማት፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ስኬታማ እንዲሆኑ ከፓርቲው ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል።

የተጀመሩ ትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች እንዲፋጠኑ የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡም እንዲሁ።

ግንቦት 24/2018 ዓ.ም በተካሔደው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ መስጠታቸውንና ድምጽ የሰጡት ፓርቲ አሸናፊ በመሆኑ ልዩ ደስታ እንደተሰማቸው የተናገሩት የሀዋሳ ከተማ ነዋሪው አቶ ምርጋ ሃርሶ ናቸው።

ፓርቲው መንግስት መስርቶ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ሊሰራ ያቀዳቸው ተግባራት እንዲሳኩ እንደ ዜጋ የሚጠበቅብኝን ሁሉ እወጣለሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም