ከፓርቲው ጋር በመሆን የተጀመሩ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንሰራለን- የሐረር ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ከፓርቲው ጋር በመሆን የተጀመሩ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንሰራለን- የሐረር ከተማ ነዋሪዎች
ሐረር ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር በመሆን የተጀመሩ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንሰራለን ሲሉ የሐረር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሕዝብ ተወካዮች እና የክልል ምክር ቤቶች ብልጽግና ፓርቲ አብላጫውን መቀመጫ በማግኘት ማሸነፉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትናንት አስታውቋል።
በዚህም መሰረት ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የሐረር ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት፤ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር በመሆን የተጀመሩ የልማት ስራዎችን አጠናክረው ለማስቀጠል ይሰራሉ ።
ከአስተያየት ከሰጡት ነዋሪዎቹ መካከል አቶ ጀማል መሐመድ እንዳሉት፤ ብልጽግና ፓርቲ በኮሪደር ልማት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በአረንጓዴ አሻራና በሌሎች የልማት ስራዎች ተጨባጭ ለውጦችን እያስመዘገበ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህንን ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ጠቁመው፤ ህዝቡም ከፓርቲው ጋር በመሆን የተጀመረውን ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
አካል ጉዳተኛው አቶ ኢምራን አህመድ በበኩላቸው፤ ፓርቲው በማሸነፉ መደሰታቸውን ተናግረው፤ ቀጣይ አምስት ዓመታት ፓርቲው የተሻለ ስራ የሚያከናውንበት መሆኑን ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው የሕዝብን ተጠቃሚነት ይበልጥ በሚያጎለብት መልኩ በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተሳትፈን ድምጻችን ዋጋ እንዳለው በግልጽ አይተናል፤ ብልጽግና ፓርቲ በማሸነፉም ተደስተናል ያለችው ደግሞ ወጣት የአብስራ ደሳለኝ ናት።
ፓርቲውም በቀጣይ አምስት ዓመታት የተሻለ ስራ እንደሚያከናውን ያላትን ተስፋ በመግለጽ “እኔም እንደ ወጣት የሚጠበቅብኝን አስተዋጽኦ አበረክታለሁ” ብላለች፡፡
ወጣት አብዱለዚዝ ሸኪብ በበኩሉ "ብልጽግና ፓርቲ ሀገሪቱን ወደፊት እያሻገረ የሚገኝ ፓርቲ ነው፤ በዚህም በቀጣይ አምስት ዓመት የተሻለ የልማት ተግባራትን በማከናወን የህዝብ ተጠቃሚነትን ያጎለብታል የሚል እምነት አለኝ" ብሏል።
ፓርቲው በርካታ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በመገንባትና በመፈጸም “ቃልን በተግባር አሳይቷል” ያለው ወጣት አብዱለዚዝ፤ በቀጣይም ከፓርቲው ጋር የተጀመረውን የልማት ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን ብሏል።
የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመጨረሻ ውጤት ይፋ መሆኑን ተከትሎ አሸናፊ የሆነው ብልፅግና ፓርቲ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ምስጋና አቅርቧል።