ህዝቡ የጣለብንን ታላቅ ኃላፊነት ከግብ ለማድረስና የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ በትጋት እንሰራለን - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ህዝቡ የጣለብንን ታላቅ ኃላፊነት ከግብ ለማድረስና የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ በትጋት እንሰራለን - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦ህዝቡ የጣለብንን ታላቅ ኃላፊነት ከግብ ለማድረስ፣ አብሮነትን ለመገንባትና የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ በትጋት እንሰራለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአራዳ የበጎነት መንደር የአቅመ ደካሞችና የሀገር ባለውለታዎች የመኖሪያ ቤት ግንባታ የማስጀመሪያ መርሃግብር ተካሂዷል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ፣ የከተማዋ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ፣ የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች፣ ባለሃብቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ ሀደሲንቄዎች እንዲሁም የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ የአራዳ በጎነት መንደር ግንባታ ህብረተሰቡ የጣለብንን እምነትና የሰጠንን ድምፅ የቃልኪዳን ውል አድርገን በተቀበልን ማግስት መጀመሩ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
ግንባታው "ገዳም ሰፈር" ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚከናወን የመልሶ ማልማት ስራ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባዋ፣ በመጀመሪያው ምዕራፍ ባለዘጠኝ ወለል ዘመናዊ የመኖሪያ ህንፃ እና ባለአራት ወለል የገበያ ማዕከል ግንባታ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።
የገዳም ሰፈር አካባቢ ቀደም ሲል ለኑሮ ምቹ ያልሆኑ፣ ያልዘመኑና ከተማዋን የማይመጥኑ ቤቶች የነበሩበት ቢሆንም፤ ታሪካዊ ቅርሶች ያሉበትና በርካታ ቱሪስቶችን የሚያስተናግድ ስፍራ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም ይህ የአራዳ በጎነት መንደር ለህብረተሰቡ ምቹ የመኖሪያ አካባቢን ከመፍጠር ባለፈ፣ የነዋሪዎችን ኑሮና አኗኗር በእጅጉ የሚያሻሽል መሆኑን ገልፀዋል።
ባለፉት ዓመታት በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ ሆነን ውጥኖቻችንን በማሳካት ውጤት አስመዝግበናል ያሉት ከንቲባዋ ውብ፣ ፅዱ፣ አረንጓዴና ለነዋሪዎች ምቹ ከተማን ለመፍጠር የጀመርነው የ24/7 ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በከተማዋ የበጎነት እሴት ከቀን ወደ ቀን እየጎለበተ መምጣቱን የገለጹት ከንቲባዋ፣ ይህ የበጎነት መንደርም ከተማ አስተዳደሩ ከባለሃብቶች ጋር በመተባበር የሚገነባው መሆኑን አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም በ2018 የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 2 ሺህ 500 የመኖሪያ ቤቶችን ከመገንባት ባለፈ ሌሎች በርካታ የበጎ ተግባር ስራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ የሕብረተሰብ ተሳትፎና የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽነር አቶ ይመር ከበደ በበኩላቸው፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በከተማዋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ በርካታ አካላት በንቃት እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ከ46 ሺህ በላይ ቤቶች ተገንብተው ከ200 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል።
ለዚህም ስራ ስኬት ከ55 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት በበጎ ፈቃደኞች አማካኝነት በገንዘብ፣ በእውቀትና በጉልበት ማዋል መቻሉን አብራርተዋል።
በ2018 የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የነዋሪዎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የተለያዩ መርሃግብሮች ተቀርፀው ወደ ትግበራ እንደሚገቡም አስታውቀዋል።
የአራዳ ክፍለ ከተማ ስራ አስፈፃሚ ወንድሙ ዑመር በበኩላቸው፤ የሚከናወነው ግንባታ አካባቢውን ለሰው ልጆች ክብር በሚመጥን መልኩ የሚያዘምን ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም አካባቢያቸው ለኑሮ አመቺ እንዳልነበር የገለፁት ደግሞ የአካባቢው ነዋሪዎች ናቸው።
ዛሬ ግን ክረምት ቢሆንም ለገዳም ሰፈር መስከረም ጠባ ፀሀይም ወጣላት ያሉት ነዋሪዎቹ ግንባታው ተጠናቆ የዘመነ ኑሮ ለመኖር ተስፋን እንደጫረባቸውም ተናግረዋል።