ብልጽግና ፓርቲ አብላጫ የምክር ቤቶች መቀመጫ በማግኘት አሸናፊ መሆኑ የተጀመሩ ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎችን ለስኬት ለማብቃት ዕድል ይፈጥራል - ኢዜአ አማርኛ
ብልጽግና ፓርቲ አብላጫ የምክር ቤቶች መቀመጫ በማግኘት አሸናፊ መሆኑ የተጀመሩ ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎችን ለስኬት ለማብቃት ዕድል ይፈጥራል
ወልቂጤ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦ብልጽግና ፓርቲ አብላጫ የምክር ቤቶች መቀመጫ በማግኘት አሸናፊ መሆኑ የተጀመሩ ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎችን ለስኬት ለማብቃት ዕድል ይፈጥራል ሲሉ የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ መንግስት ለመመስረት የሚያስችለውን አብላጫ የምክር ቤት መቀመጫ ማግኘቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትናንት ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
በእዚህም ፓርቲው ለሕዝብ ተወካዮች እና ለክልል ምክር ቤቶች አብላጫውን መቀመጫ በማግኘት ማሸነፉን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫውን ውጤት ይፋ ማድረጉን ተከትሎ የኢዜአ ሪፖርተር በወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎችን አነጋግሯል።
ነዋሪዎቹ ፤ በምርጫው ከጅምሩ እስከመጨረሻው የታየው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሂደት በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርአት ጥሩ መሰረት እየያዘ መምጣቱን ያመላከተ ነው ብለዋል።
በምርጫው ቀን ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም ከማለዳ እስከ እኩለሌሊት ረጃጅም ሰልፎችን ታግሰው ድምጽ እንደሰጡ አስታውሰው፣ በዚህም ደስተኞች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ ሀይሉ ተሰማ፣ ወይዘሪት ሳድያ ኑረዲን እና አቶ መንግስቱ ባንቀስራ፤ በምርጫው ብልጽግና ፓርቲ አብላጫ የምክር ቤት መቀመጫ በማግኘት አሸናፊ መሆኑ ባለፉት ዓመታት የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለስኬት ለማብቃት መልካም እድል መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በብልጽግና ፓርቲ የተመራው መንግስት ያከናወናቸው የልማት ሥራዎች ለኢትዮጵያ እድገትና ማንሰራራት መሰረት ያኖሩ መሆኑን አንስተው በቀጣይ ለላቀ ስኬት መትጋት እንዳለበት ተናግረዋል።
በተለይም የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲሳኩ፣ የከተሞችና የገጠር ኮሪደር ልማት ቀጣይነት እንዲኖረው እንዲሁም ለግብርና ምርታማነት ማደግ ብዙ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም ለሀገር ልማት ስኬትና እድገት የመንግስት ጥረት ብቻውን በቂ ባለመሆኑ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማድረግ ተዘጋጅተናል ብለዋል።
የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና እድገት እውን ለማድረግ ከመንግስት ጋር በተደመረ አቅምና በተባበረ ክንድ መስራት ይኖርብናል ሲሉም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።