ብልጽግና ፓርቲ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት አጠናክሮ ሊያስቀጥል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ብልጽግና ፓርቲ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት አጠናክሮ ሊያስቀጥል ይገባል
ባህር ዳር ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦ ብልጽግና ፓርቲ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት አጠናክሮ ሊያስቀጥል ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ገለጸ።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሕዝብ ተወካዮች እና በክልል ምክር ቤቶች ብልጽግና ፓርቲ አብላጫውን መቀመጫ በማግኘት ማሸነፉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
ይህንንም ተከትሎ ፓርቲው ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ምስጋና አቅርቦ ሁለንተናዊ ብልፅግናን በተግባር የማረጋገጥ ታሪካዊ ጉዞውን ከምንጊዜውም በላይ በበለጠ ትጋት፣ በአንድነትና በቁርጠኝነት አጠናክሮ እንደሚያስቀጥልም ቃል ገብቷል።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ፍሬሰላም ዘገዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ብልጽግና ፓርቲ አብላጫ ድምፅ በማግኘት ለቀጣይ አምስት ዓመታት ሀገር የመምራት እድል በማግኘቱ ደስታ ተሰምቷቸዋል።
"በክልሉ ከአራት ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች ይገኛሉ" ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የአካል ጉዳተኞች ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ከማድረግ ባሻገር በመምረጥ ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በዚህም አሸናፊው ብልጽግና ፓርቲ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት አጠናክሮ ሊያስቀጥል ይገባል ብለዋል።
በተለይም ፓርቲው አካል ጉዳተኞችን ወደ ውሳኔ ሰጪነት እንዲመጡ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በኩል ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ የበኩላቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።
በየደረጃው ባለ የመንግስት እርከን የአካል ጉዳተኞችን ፍላጎት ያማከለ ውክልናን ለማስፈን ከአሸናፊው ብልጽግና ፓርቲ ጋር በመተባበር ፌዴሬሽኑ ይሰራል ብለዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱን ምቹ፣ ተደራሽና አካታች በማድረግ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ማስፈን የአሸናፊ ፓርቲው ዋነኛ የቤት ሥራ መሆኑን አስረድተዋል።
የአካል ጉዳተኞችም ድጋፍ እንዲደረግላቸው መጠየቅ ብቻ ሳይሆን፣ በሀገራቸው ሰላምና ልማት ላይ የላቀ አበርክቶ እንዲኖራቸው ተቀናጅተው እንደሚሰሩም ቃል ገብተዋል።
በአካል ጉዳተኞች ዘንድ ያለውን እውቀት፣ ጥበብና አቅም ለህብረ ብሔራዊ አንድነትና ጠንካራ ሃገረ መንግስት ግንባታ ለማዋል በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም አክለዋል።