ቀጥታ፡

ፓርቲው በጠቅላላ ምርጫው ማሸነፉ የተጀመሩ ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶችን ዳር ለማድረስ ዕድል የሚፈጥር ነው

ጭሮ/ነጌሌ ቦረና/ጊምቢ ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦ የብልፅግና ፓርቲ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ማሸነፉ የጀመራቸውን ግዙፍ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥርለት የኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች ገለፁ።

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሕዝብ ተወካዮች እና የክልል ምክር ቤቶች ብልጽግና ፓርቲ አብላጫውን መቀመጫ በማግኘት ማሸነፉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

የብልፅግና ፓርቲ ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት እና የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ሲንቀሳቀስ መቆየቱ ይታወቃል።

በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ በኮሪደር ልማት፣ በግብርናው ዘርፍ  እንዲሁም በቱሪዝምና በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ረገድ ሀገራዊ ለውጥ የሚያመጡ ሰፋፊ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።

ፓርቲው እነዚህን ፕሮጀክቶች በተቀናጀ እና በተሟላ ሁኔታ ለማስቀጠል እንዲሁም ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚያስችለውን የህዝብ ይሁንታ አግኝቷል።

ነዋሪዎቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ በተለይ በዚህ ዓመት የተጀመሩ ትላልቅ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ለውጥ የሚያረጋግጡ በመሆናቸው፣ አሸናፊው ብልፅግና ፓርቲ ፕሮጀክቶቹን በፍጥነት ለማጠናቀቅ በትኩረት ሊሰራ ይገባል።

የጭሮ ከተማ ነዋሪ አቶ ቡሹራ ጁሃር እንዳሉት፤ ብልፅግና ፓርቲ የጀመራቸውን እንደ ማዳበሪያ ፋብሪካ፣ ዘመናዊ አውሮፕላን ማረፊያ እና የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ልማት ያሉ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ማብቃት አለበት።

"በምርጫ ማሸነፍ ታላቅ ህዝባዊ አደራ መሸከም ነው፤" ያሉት አቶ ቡሹራ፣ በዚህ ረገድ የህዝቡን የልማት ፍላጎቶችና ጥያቄዎች ለመፍታት ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸዋል።

አክለውም በምርጫው አብላጫ ድምፅ በማጣት የተሸነፉ ፓርቲዎችም የሀገሪቱን ዕድገትና ለውጥ ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የከተማው ነዋሪ አቶ አሚን አሊዪ በበኩላቸው፤ ብልፅግና ፓርቲ በምርጫው ማሸነፉ የሀገር አንድነትን ለማጠናከር፣ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈንና የበለፀገች ሀገር ለመፍጠር የጀመረውን ጥረት እንዲያሳካ ዕድል እንዳስገኘለት ተናግረዋል።

ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የምርጫ ውጤቱን በጋራና በፀጋ በመቀበል፣ ከተመራጩ ፓርቲ ጋር ሀገሪቱን ለማሸጋገር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

ያህያ አደም በበኩሉ፤ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘውን ዳግም ዕድል በመጠቀም በግብርና፣ በከተሞች ልማት እና በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ያስመዘገበውን ውጤት በማጠናከር ሀገሪቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ተግቶ ሊሰራ እንደሚገባ ገልጿል።

ነዋሪዎቹ በሁሉም መስኮች ሀገሪቱን ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ብልፅግና ፓርቲ ለሚያደርገው ጥረት ድጋፋቸውን እንደሚሰጡም አረጋግጠዋል።

የነጌሌ ቦረና ከተማ ነዋሪዎችም የፖለቲካ ፓርቲዎች የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ውጤት በጸጋ በመቀበል ለሀገር ልማትና እድገት በትብብር እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

በከተማው የሀሎ ጋፍትሮ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ገመቹ ገቢስ፤ ዴሞክራሲያዊና አሳታፊ ምርጫ መካሄዱን ጠቅሰው፣ አሸናፊው ፓርቲ ብዙ ስራ እንደሚጠበቅበት አውቆ መንቀሳቀስ አለበት ብለዋል።

የዚሁ ከተማ የመልካ ኦዳ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ወንዶሰን ፈለቀ በበኩላቸው፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ ለመስጠት ከጠዋቱ 11 ሰዓት ጀምሮ የነበረው ህዝባዊ ሰልፍ በታሪክ የማይረሳ ክስተት እንደነበርም አስታውሰዋል።

በምርጫው ያልተሳካላቸው ፓርቲዎችም ውጤቱን በጸጋ በመቀበል ህዝባቸውንና ሀገራቸውን ሊያስቀድሙ እንደሚገባና አሸናፊው ፓርቲም የተቀበለውን የህዝብ አደራ ለመወጣት መትጋት አለበት ብለዋል።

የምዕራብ ወለጋ ዞን ነዋሪዎችም ብልጽግና ፓርቲ ህዝብን ማዕከል ባደረጉ የመሰረተ ልማት ስራዎች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባው ገልጸዋል።

የእናንጎ ከተማ ነዋሪ አቶ አድማሱ ታመነ እንዳሉት፤ አሸናፊው ፓርቲ በቀጣይ ትኩረት የሚሹ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ይመልሳል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የላሎ አሳቢ ወረዳ ነዋሪ አቶ ባህሩ ኢማና በበኩላቸው፤ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ቃል የተገቡልን ልማቶች በተግባር እንዲፈጸሙ ከተመራጩ ፓርቲ እንጠብቃለን ሲሉ ገልጸው፤ ፓርቲው ለማከናወን ላቀዳቸው የልማት ስራዎች ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም