ቀጥታ፡

ከአውሮፓ እና ደቡብ አሜሪካ እጅ ወጥቶ የማያውቀው የዓለም ዋንጫ ክብር

በሙሴ መለሰ 

እግር ኳስ በዓለም ላይ ተወዳጅ ከሆኑ ስፖርቶች መካከል አንዱ ነው።  በየአራት ዓመቱ የሚካሄደው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ አፍቃሪያን ትኩረት የሚስብ ግዙፍ ውድድር መሆኑ ይታወቃል።

የዓለም ዋንጫ ትልቁ ስፖርታዊ ሁነት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ይህ ግዙፍ ሁነት መካሄድ ከጀመረ አንድ ክፍለ ዘመን ሊያስቆጥር ነው።

እ.አ.አ በ1930 የመጀመሪያው ዓለም ዋንጫ ኡራጓይ አስተናጋጅነት ተከናውኗል። በወቅቱ አዘጋጇ ሀገር አርጀንቲናን በመርታት ታሪካዊውን ዋንጫ አንስታለች።

እስከ አሁን በተደረጉ 22 የዓለም ዋንጫዎች 80 ሀገራት የተሳተፉ ሲሆን ከነዚህ ውሰጥ ዋንጫ ማንሳት የቻሉት ስምንት ሀገራት ብቻ ናቸው።

ብራዚል፣ ጀርመን፣ ጣልያን፣ አርጀንቲና፣ ፈረንሳይ፣ ኡራጓይ፣ እንግሊዝ እና ስፔን ዋንጫውን ያነሱ ሀገራት ናቸው።

በውድድሩ የ96 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ዋንጫው ከአውሮፓ እና ደቡብ አሜሪካ ሀገራት እጅ ወጥቶ አያውቅም።


 

ከዚህም ባለፈ በነዚህ አህጉራት ከሚገኙ ሀገራት ውጪ ለፍጻሜ አልፎ የሚያልቅ ብሔራዊ ቡድን አለመኖሩ ሌላኛው ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ነው። 

ከ22ቱ የዓለም ዋንጫዎች 12ቱ ወደ አውሮፓ ሀገራት አምርተዋል።  የደቡብ አሜሪካ ሀገራት 10 ጊዜ ዋንጫውን አንስተዋል። 

ብራዚል አምስት ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ስኬታማዋ ሀገር ናት። 
 
ጀርመን እና ጣልያን በተመሳሳይ አራት ጊዜ ውድድሩን በማሸነፍ ይከተላሉ።

አርጀንቲና ሶስት ጊዜ ዋንጫውን ማንሳት ችላለች። የወቅቱም የውድድሩ አሸናፊ ናት።

ፈረንሳይ እና ኡራጓይ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ዋንጫውን አንስተዋል። እንግሊዝ እና ስፔን በተመሳሳይ አንድ ጊዜ የዋንጫ ባለቤት ሆነዋል። 

በዓለም ዋንጫው ከሰባት አህጉራት የተወጣጡ ሀገራት እየተሳተፉ ቢገኝም አሸናፊነቱ ከአውሮፓ እና ደቡብ አሜሪካ አለመውጣቱ የሁለቱን አህጉራት ፍጹም የበላይነት የሚያሳይ ነው።

23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በአሜሪካ፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ ጣምራ አዘጋጅነት እየተካሄደ ይገኛል። 

በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 48 ሀገራት እየተሳተፉ ይገኛል። 

በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ከደቡብ አሜሪካ እና አውሮፓ ሀገራት ወጥቶ የሌላ አህጉር ቡድን ያሸነፍ ይሆን?  የሚለው ጉዳይ ትኩረትን ስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም