የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 36ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 36ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 36ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ፋሲል ከነማ ከአርባምንጭ ከተማ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
በ35ኛው ሳምንት ሀዲያ ሆሳዕናን 1 ለ 0 የረታው ፋሲል ከነማ በ49 ነጥብ ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
አርባምንጭ ከተማ በ35 ነጥብ 20ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ቡድኑ ባለፉት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል አስመዝግቧል።
ጨዋታው ፋሲል ከነማ በድል ጉዞው ለመቀጠል አርባምንጭ ከተማ ከመውረድ ለመትረፍ እያደረገው ባለው ጉዞ ሶስት ነጥብ ለማግኘት የሚያደርጉት ነው።
በሌላኛው መርሐ ግብር ወላይታ ድቻ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ወላይታ ድቻ በ47 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል። ተጋጣሚው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በተመሳሳይ 47 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በ35ኛ ሳምንት ባህር ዳር ከተማን 2 ለ 0 ያሸነፈው ወላይታ ድቻ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።
በአንጻሩ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻለው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የድልን መንገድን ለማግኘት ይፋለማል።
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከሀዲያ ሆሳዕና ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ባለፉት ሶስት የሊጉ ጨዋታዎች አቻ የተለያየው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ42 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዟል።
ሀዲያ ሆሳዕና በ43 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቡድኑ ካለፉት ሶስት ጨዋታዎች ሶስት ነጥብ ማግኘት አልቻለም።
ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚጫወቱ ሲሆን ሶስት ነጥብ የሚያገኘው ቡድን በሊጉ መቆየቱን የሚያረጋግጥበት እድል ሊኖር ይችላል።
በተያያዘም ትናንት በመብራት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ምድረ ገነት ሽሬ መርሐ ግብር ቀሪ ስድስት ደቂቃ ከረፋዱ አራት ሰዓት አንስቶ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይደረጋል።
ጨዋታው እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ግብ አልተቆጠረም።