የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን የጋራ ውጤት ነው-ምርጫ ቦርድ - ኢዜአ አማርኛ
የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን የጋራ ውጤት ነው-ምርጫ ቦርድ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 14/2018 (ኢዜአ)፦የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ መራጮችና የሌሎች ባለድርሻ አካላት የጋራ ውጤት መሆኑን የኢትዮጵያውያን የጋራ ውጤት መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ይፋ አድርጓል።
በዚህም ቦርዱ እንዳሳወቀው፤ ብልጽግና ፓርቲ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ ከተሰጠባቸው እና ውጤታቸው ይፋ ከሆኑ የምርጫ ክልሎች አብላጫ ድምጽ አግኝቷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ የሲቪል ማህበራት ተወካዮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ሁሉ በተለየ መልኩ ከቅድመ ምርጫ እስከ ድህረ ምርጫ በራስ አቅም የተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ አካታችነትን ዋና የትኩረት ማዕከሉ አድርጎ መሥራቱን በመጥቀስ፥ በተለይ የአካል ጉዳተኞች እና የሴቶች የነቃ ተሳትፎ እንደታየበት አመላክተዋል፡፡
ለምርጫው መሳካት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት፣ የአፍሪካ ህብረትና የኢጋድ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ተሳትፎ አስደናቂ እንደነበር አስረድተዋል።
በፀሐይና በዝናብ ሳይበገሩ በትዕግስት ተሰልፈው ድምጻቸውን የሰጡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መራጮች፣ የጸጥታ አካላትና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ለምርጫው ስኬታማ ፍጻሜ ገንቢ ሚና መወጣቱን ገልጸዋል።
የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ መራጮችና የሌሎች ባለድርሻ አካላት የጋራ ውጤት መሆኑን አንስተዋል።
በምርጫው የአፍሪካ ህብረት ከ60 በላይ ታዛቢዎችን በማሰማራት የምርጫውን ዴሞክራሲያዊነት ታዝቧል ያሉት ደግሞ የህብረቱ የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደህንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ ናቸው።
ኢትዮጵያዊያን በሰባተኛ ጠቅላላ ምርጫ ያሳዩት ተሳትፎ ለስኬታማ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ትልቅ እርምጃ መጀመራቸውን በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህ ስኬትም የአፍሪካ ህብረት ትልቅ አድናቆት እንዳለው አረጋግጠዋል።
የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራቱ ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር በሚያደርጉት ጉዞ ፍጹም ገለልተኛ፣ ሚዛናዊ እና ነጻ በሆነ መንገድ የመደገፍ ግዴታ እንዳለው ተናግረዋል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በታዛቢነት የተሳተፈው የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ዋና ዳይሬክተር ሕብረት አባሆይ፤ በምርጫው ላይ ሴቶች ያለምንም ስጋት ሕገ-መንግስቱ የሰጣቸውን ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲጠቀሙ ከተለያዩ አካላቶች ጋር መሰራቱን አስታውሰዋል።
በታዛቢነት በተሰራው ሥራም ሴቶች ደህንነታቸው ተጠብቆ ይበጀኛል ለሚሉት አካል ድምጻቸውን መስጠት እንደቻሉ ትዝብት መወሰዱን አስረድተዋል።
የምርጫ ጣቢያዎችም ለነፍሰ ጡሮች፣ ለሚያጠቡ እናቶች፣ ለአረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞችና ሌሎች ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች ምቹና አካታች ምኅዳር መፈጠሩን አረጋግጠናል ብለዋል።