ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ እድገትና ማንሰራራት ለማስቀጠል ብልጽግና ፓርቲ ይበልጥ መትጋት አለበት - ነዋሪዎች

ወላይታ ሶዶ፤ ሰኔ 14/2018(ኢዜአ)-በብልጽግና ፓርቲ የሚመሰረተው መንግስት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ እድገትና ማንሰራራት ለማስቀጠል ይበልጥ መትጋት አለበት ሲሉ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ መንግስት መመስረት የሚያስችለውን አብላጫ የምክር ቤት መቀመጫ ማግኘቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ አድርጓል።

የምርጫው ውጤት ይፋ መደረጉን ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች፤ በምርጫው ያሳየነውን ተሳትፎ በቀጣይ በልማት ሥራዎች ላይ በመድገም ሀገራችንን ከድህነትና ከተረጂነት ማውጣት ይጠበቅብናል ብለዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ ታፈሰ ጭርቦ እና አቶ በቀለ ግምጃያ፤ በኢትዮጵያ በከተሞችም ይሁን በገጠር የዜጎችን ተጠቃሚነትና የሀገር እድገት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶች ውጤታማ መሆናቸውን አንስተዋል።

በከተሞች ማራኪ የሆኑ የመኖሪያ አካባቢዎችን በመፍጠር፤ በገጠርም የአርሶ አደሩን ህይወት ለማሻሻል የተጀመሩ ስራዎች እንዲሁም በግብርና ልማት የተጀመሩ ጥረቶች ለሀገራችን ትልቅ ተስፋ የሰነቁ ናቸው ብለዋል።

በመሆኑም በሀገሪቷ የተጀመሩ ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ብልጽግና ፓርቲ ማሸነፉ መልካም አጋጣሚ መሆኑን አንስተው፣ በቀጣይም ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት አስተዋጽኦ ለማድረግ ተዘጋጅተናል ሲሉ ተናግረዋል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ትርንጎ ቱማቶ እና ተማሪ ተመስገን ምትኩ፤ በምርጫው የነበራቸውን ጠንካራ ተሳትፎ በልማትም ለመድገም አሸናፊውን ፓርቲ ለማገዝ  መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ 42 የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ የምርጫ ፉክክር ማድረጋቸው የሚታወቅ ነው።

በምርጫው ለሕዝብ ተወካዮች እና ለክልል ምክር ቤቶች ብልጽግና ፓርቲ አብላጫውን መቀመጫ በማግኘት ማሸነፉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ አድርጓል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም