የዘመናችን ዴሞክራሲ አስተምህሮቱ ሰላም ቋንቋውም ምርጫ ነው -ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
የዘመናችን ዴሞክራሲ አስተምህሮቱ ሰላም ቋንቋውም ምርጫ ነው -ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 14/2018 (ኢዜአ)፦ የዘመናችን ዴሞክራሲ አስተምህሮቱ ሰላም ቋንቋውም ምርጫ ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ።
በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ድምጻቸውን የሰጡበት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እስከ እኩለ ሌሊት መካሄዱ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫውን ውጤት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በተገኙበት ይፋ አድርጓል።
ፕሬዝደንት ታዬ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አዲስ የፖለቲካ ልምምድ ስር እንደሰደደ አይተንበታል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ምርጫው ከፍተኛ የህብረተሰቡ ተሳትፎ የታየበት ነው ብለዋል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ማህበራዊ ዕሴታቸውን ያሳዩበት የተዋበ መድረክ እንደነበር ተናግረዋል።
እያንዳንዱ የተሰጠ ድምጽም ከዜጎች የተሰጠ አደራ እና የክብር ማህተም መሆኑን ጠቁመው፤ ድምጽ ያገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይህንን አደራ መጠበቅ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የዘመናችን ዴሞክራሲ አስተምህሮቱ ሰላም ቋንቋውም ምርጫ መሆኑን አጽንኦት የሰጡት ፕሬዚዳንቱ፤ ከምርጫ ውጭ ስልጣን የመያዝ ናፍቆት ያላቸው አካላት የማይሳካ መንገድ መያዛቸውን መገንዘብ እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የተሳሳተ መንገድን የተከተሉ አካላት አካሄዳቸው ስሁት መሆኑን ማሳየቱን አስረድተዋል።