ቀጥታ፡

ብልፅግና ፓርቲ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አብላጫ የምክርቤት መቀመጫ ማግኘቱ መንግስት የጀመራቸውን ሀገራዊ ስራዎች ይበልጥ እንዲያሳካ አቅም ይፈጥርለታል - የሰመራ ሎጊያ ከተማ ነዋሪዎች

ሰመራ፤ ሰኔ 14/2018(ኢዜአ) ብልፅግና ፓርቲ በምርጫው አብላጫ የምክርቤት መቀመጫ አግኝቶ ዳግም መመረጡ፣ የተጀመሩ የልማትና የሰላም ሥራዎችን በላቀ ትጋትና ቁርጠኝነት ለማስቀጠል የሚያስችለው ትልቅ አቅም እንደሚሆንለት የሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ተናገሩ።

ብልፅግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት በአፋር ክልል የመሠረተ ልማት ተደራሽነትን ለማስፋፋት፣ የሰመራ ሎጊያ ከተማን ገጽታ ለመቀየር እንዲሁም የአካባቢውን የጸጥታ ሁኔታ አስተማማኝ ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱ ይታወቃል።

በተለይም በክልሉ የሚስተዋለውን የውኃ እጥረት ለመቅረፍ የተጀመሩ ግዙፍ የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች፣ የሕዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ የከተማ ግብርናና የመስኖ ልማት ሥራዎች፣ እንዲሁም የንግድና የሎጂስቲክስ ፍሰቱን የሚያቀላጥፉ ዘመናዊ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች የፓርቲው ዋነኛ የትኩረት ማዕከል ነበሩ።

የከተማ አስተዳደሩ ነዋሪዎች እንዳሉት እነዚህ የተጀመሩ ዘላቂ የልማትና የሰላም ሥራዎች ፍሬ አፍርተው እንዲጠናቀቁ ጠንካራና ሕዝባዊ መሠረት ያለው መንግሥታዊ መዋቅር እንዲቀጥል የሚያስችል ውጤት ይፋ ተደርጓል።

በዚህም መሰረት በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሕዝብ ተወካዮች እና የክልል ምክር ቤቶች ብልፅግና ፓርቲ አብላጫውን መቀመጫ በማግኘት ማሸነፉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

የምርጫውን ውጤት ይፋ መደረግ ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች፤ ብልፅግና ፓርቲ ማሸነፉ በቀጣይ ዓመታት ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸውንና ለሕብረተሰቡ የሚጠቅሙ የልማት ሥራዎችን በላቀ ፍጥነት ለማከናወን ትልቅ አቅም ይፈጥርለታል።

ከከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ አብዱ ኢሴ፤ ብልፅግና ፓርቲ በምርጫው አብላጫ ድምፅ በማግኘቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ፓርቲው ባለፉት ዓመታት ያከናወናቸው ሥራዎች የሕዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሆናቸውን ገልጸው፤ የምርጫ ውጤቱም ፓርቲው የሕዝብን አደራ በመቀበል የተጀመሩ ግዙፍ ሥራዎችን በላቀ መነሳሳት እንዲያጠናቅቅ ትልቅ እድል እንደሚፈጥርለት አስረድተዋል።

ሌላኛው የከተማው ነዋሪ አቶ ከድር ሰኢድ በበኩላቸው፤ ብልፅግና ፓርቲ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አብላጫ ድምፅ በማግኘቱ፥ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን በፍጥነት አጠናቆ ለሕብረተሰቡ ተጠቃሚነት ለማዋል ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

በምርጫ ውጤቱ ደስታቸውን የገለፁት ነዋሪው፤ ፓርቲው በቀጣይነት ለህዝብ ጥቅም ሊሰጡ የሚችሉ ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባው ነው የገለፁት።

ብልፅግና ፓርቲ ለህብረተሰብ ጠቃሚ የሆኑ የልማት ስራዎችን እያከናወነ ነው ያሉት ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ዓሊ ሁሴን ናቸው።

ከዚህም የበለጠ አጠናክሮ መቀጠል እንዲችልና የተሻሉና ተጠቃሚነትን የሚጨምሩ ፕሮጀክቶችን ማከናወን እንዲችል የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም