ቀጥታ፡

አሸናፊው ፓርቲ በምርጫ ወቅት የገባውን ቃል በመፈጸም የህዝብ ተጠቃሚነትን በተግባር ማሳየት አለበት

አዳማ፤ ሰኔ 14/2018 (ኢዜአ)፡-በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያሸነፈው ፓርቲ በምርጫ ወቅት የገባውን ቃል በመፈጸም የህዝብ ተጠቃሚነትን በተግባር ማሳየት አለበት  ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች  ተናገሩ።

በኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት መሠረት በየአምስት ዓመቱ የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ፣ የሕዝብን የሥልጣን ባለቤትነትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ለማረጋገጥ የሚደረግ ትልቅ ሀገራዊ ሁነት ነው። 

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝብን ድምፅ ለማግኘትና የዜጎችን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ የቃል ኪዳን ሰነዶችን ይዘው መቅረባቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያሸነፈውን ፓርቲ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች እንዳሉት በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያሸነፈው ፓርቲ በምርጫ ወቅት የገባውን ቃል በመፈጸም የህዝብ ተጠቃሚነትን በተግባር ማሳየት አለበት። 

አስተያየታቸውን ከሰጡ የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ዓሊ መሀመድ እንዳሉት ምርጫውን አሸንፎ አዲስ የሚመሰረተው መንግስት የልማትና መልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን በዘላቂነት በመፍታት ለህዝብ የገባውን ቃል በተግባር ሊያሳይ ይገባል።

የ88 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ዓሊ፤ በዘመናቸው እንዲህ ዓይነት መልካም መንግሥት እንዳላዩ ተናግረዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ከለውጡ ወዲህ የህዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ በርካታ የልማት ስራዎችን ማከናወኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም የህዝብ አንገብጋቢ ከሆኑ ችግሮች መካከል  የመኖሪያ ቤት ችግርን ከመሠረቱ ለመፍታት እንዲሰራ ጠይቀዋል።

ህዝቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም የሚጠበቅበትን ድጋፍ ማድረግ ከቻለ ከዚህ የተሻለ ልማት በሀገሪቱ ሊረጋገጥ እንደሚችል ያላቸውን እምነት አጋርተውናል።

ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ ወጣት አብይ ታዬ በበኩሉ ገዢው ፓርቲ የሀገሪቱን እድገት የሚያፋጥኑ የልማት ስራዎች መስራቱን አስታውሶ ዳግም መንግሥት የመሆን እድሉን በአግባቡ በመጠቀም በቀጣይ አምስት ዓመታት ለመሥራት ያቀዳቸውን የልማት ሥራዎች ዳር ማድረስ ይጠበቅበታል ብሏል።

በተለይም ህዝብን ለምሬት የሚዳርጉ የአገልግሎት አሰጣጥና ብልሹ አሰራሮችን ፈትሾና ገምግሞ በማረምና ተጠያቂነት ያለው አሰራር በማስፈን በምርጫ ወቅት የገባውን ቃል በምርጫ ማግስት በመፈጸም የህዝብ ተጠቃሚነትን በተግባር ማረጋገጥ ይኖርበታል ነው ያለው።

ወይዘሮ መስተዋት ከፈኒ በበኩላቸው 7ኛው ጠቅላላ  ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ታማኝነት ያለው ምርጫ ሆኖ በድልና በስኬት ተጠናቆ ዛሬ ላይ ያሸነፈው ፓርቲ መታወቁ አስዳሳች መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም በምርጫው ያሸነፈው  ፓርቲ ለህዝብ የገባውን ቃል ማክበር ይጠበቅበታል ብለዋል።

በተለይም  ከምንም በላይ አስተማማኝ ሰላም እንዲያሰፍን፣ የዜጎችን የስራ አጥ ችግሮችን ለማቃለል አተኩሮ በመስራት የገባውን ቃል በተግባር እንዲያሳይ ጠይቀዋል።

በምርጫው ያሸነፈው መንግሥት ባለፉት ዓመታት በከተማዋ በርካታ የልማት ስራዎችን በመስራት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንዳደረገው ሁሉ በቀጣይም  ሀገሪቱን የሚያሻግር ስራ እንዲሰራ ያላቸውን ፍላጎት የገለጹት ደግሞ አቶ ፍቃዱ ተክሌ ናቸው። 

በተለይ ሀገሪቱን የባህር በር ባለቤት ጥያቄ እውን ከማድረግ ባሻገር በሰላምና ጸጥታ ሥራዎች፣ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በልማትና በመልካም አሥተዳደር የህዝቡን ፍላጎት እና እርካታ ያማከለ ሥራ እንዲሰራ ጠይቀዋል።

በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ወቅትና በድህረ ምርጫ የታየው ሠላምና  አንድነትን አጠናክሮ በማስቀጠል ህዝብንና ሀገር ማሻገር የሚያስችል ሥራ መሥራት አዲስ ከሚመሰረተው ምንግሥት  ይጠበቃል ሲሉም አቶ  ፍቀዱ ገልጸዋል።

እንደ አሰተያየት ሰጪዎቹ ገለፃ በምርጫው አሸናፊ ሆኖ መንግሥት የሚመሰርተው ፓርቲ የመረጠውን ብቻ ሳይሆን መላውን ህዝብ በእኩልነት ማገልገል ይጠበቅበታል። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም