ኢትዮጵያዊያን በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ያደረጉት ስኬታማ ተሳትፎ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትልቅ እርምጃ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያን በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ያደረጉት ስኬታማ ተሳትፎ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትልቅ እርምጃ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 14/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያዊያን በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ያደረጉት ስኬታማ ተሳትፎ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትልቅ እርምጃ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደህንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት የማሳወቂያ መርሃ-ግብር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ የሲቪል ማህበራት ተወካዮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በዚሁ ወቅት የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ልዑክ እና የህብረቱ የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደህንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ፤ የኢትዮጵያዊያን በሰባተኛ ጠቅላላ ምርጫ ያሳዩት ተሳትፎ ለስኬታማ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ትልቅ እርምጃ መጀመራቸውን በተግባር ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
ለዚህም ለሚያደርጉት ስኬታማ ጉዞ የአፍሪካ ህብረት ትልቅ አድናቆት እንዳለው አረጋግጠዋል።
የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራቱ ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር በሚያደርጉት ጉዞ ፍጹም ገለልተኛ፣ ሚዛናዊ እና ነጻ በሆነ መንገድ የመደገፍ ግዴታ እንዳለበት ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ዑሁሩ ኬንያታ የሚመራ የህብረቱ የምርጫ ታዛቢ አሰማርቶ እንደነበር አስታውሰዋል።
ከሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ማግስትም የአፍሪካ ህብረት ልዑክ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርትን በማስመልከት መግለጫ ማውጣቱን አስረድተዋል።
ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር የነበረው ግንኙነት አድናቆታቸውን ገልጸው፤ በዚህች ታላቅ ሀገር ቀጣይነት ላለው መሻሻልና ለዴሞክራሲ መጎልበት በጋራ ለመስራት ቃል እንገባለን ብለዋል።
የአፍሪካ ህብረት ለኢትዮጵያ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ ግንባታ ያለውን የማይናወጥ ቁርጠኝነት በድጋሚ እንደሚያጸናም አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ሁሉም የአፍሪካ ሀገራትና ባለድርሻ አካላት ሰላማዊ፣ አካታችና ሙሉ ተሳትፎ የሰፈነበት ዴሞክራሲን ለማስፈን ቁርጠኛ ሆነው እንዲቀጥሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አህጉራችን ዴሞክራሲን ከመቀበል ውጪ ሌላ አማራጭ የላትም፤ ልማትን፣ ሰላምንና ዘላቂ ህዝባዊ እድገትን ወደፊት ለማምጣት ከሁሉ የተሻለ መንገድ ነው ብለዋል።