ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ሴቶች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም ንቁ ተሳትፎ አደርገዋል - ሕብረት አባሆይ

አዲስ አበባ፤ሰኔ 14/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ሴቶች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ዋና ዳይሬክተር ሕብረት አባሆይ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት የማሳወቂያ መርሃ-ግብር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ የሲቪል ማህበራት ተወካዮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በታዛቢነት ከተሳተፉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መካከል  የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ይገኝበታል።

የማኅበሩ ዋና ዳይሬክተር ሕብረት አባሆይ፤ ማህበሩ በምርጫው ላይ የታዘባቸውን ቁምነገሮች በማስመልከት በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ማሳወቂያ መርሃ-ግብር ላይ አብራርተዋል።

በማብራሪያቸውም፤ በኢትዮጵያ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ሴቶች ያለምንም ስጋት ሕገ-መንግስቱ የሰጣቸውን ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲጠቀሙ ከተለያዩ አካላቶች ጋር መሰራቱን አስታውሰዋል።

ምርጫው ሂደትም ከቅድመ ምርጫ እስከ ምርጫው ዕለት ድረስ ሴቶች ደህንነት ተጠብቆ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ለማድረግ አበረታች ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።

በታዛቢነት በተሰራው ሥራም ሴቶች ደህንነታቸው ተጠብቆ  ይበጀኛል ለሚሉት አካል ድምጻቸውን መስጠት እንደቻሉ ትዝብት መወሰዱን አስረድተዋል።

የምርጫ ጣቢያዎችም ለነፍሰ ጡሮች፣ ለሚያጠቡ እናቶች፣ ለአረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞችና ሌሎች ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች ምቹና አካታች ምኅዳር መፈጠሩን አረጋግጠናል ብለዋል።

ለጠቅላላ ምርጫው ስኬታማነትን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ አጋር አካላትና መንግሥትና ባለድርሻ አካላት በትብብር ለአንድ ዓላማ በቅንጅት መሰራቱንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 42 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳታፉበትና በርካታ ሚሊዮን ዜጎች ድምፅ የሰጡበትን ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ  ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም አካሂዷል።

የድምፅ መስጫ ሂደት ባልተጠናቀቀባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ድምፅ የመስጠት ሂደትም እስከ ዕኩለ ለሊት 6:00 ሰዓት ድረስ ተራዝሞ መራጮች ድምጻቸውን ሰጥተዋል።

በቦርዱ የምርጫ ዕውቅና የተሰጣቸው ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በምርጫ ታዛቢነት እንዲሁም በመራጮች ትምህርትና ስልጠና ስኬታማ ተሳትፎ አድርገዋል።

የአፍሪካ ህብረት እና የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ቡድኖችም ኢትዮጵያዊያን በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር በማሳየት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ስኬታማና ሰላማዊ ምርጫ ማካሄዳቸውን አረጋግጠዋል።

ጠቅላላ ምርጫው በ1ሺህ 139 ምርጫ ክልሎች ላይ የተካሄደ ሲሆን ከዚህም ውስጥ የ501 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በክልል ምክር ቤት ከ638 የምርጫ ክልሎች ላይ መካሄዱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም