ቀጥታ፡

ሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ግልፅነቱን ጠብቆ የተካሄደ መሆኑን ታዝበናል - የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ዋና ዳይሬክተር ሕብረት አባሆይ

አዲስ አበባ፤ሰኔ 14/2018 (ኢዜአ)፦ሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ስርዓት ያለውና ግልፅነቱን ጠብቆ የተካሄደ መሆኑን እንደታዘቡ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ዋና ዳይሬክተር ሕብረት አባሆይ ገለጹ።

በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ድምጻቸውን የሰጡበት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እስከ እኩለ ሌሊት መካሄዱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም የምርጫውን አጠቃላይ ውጤት ይፋ ማድረጊያ መርኃ ግብር ላይ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ የሲቪል ማህበራት ተወካዮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአዲስ አበባ እያካሄደ ይገኛል።

የሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ከታዘቡ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበራት መካከል የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ዋና ዳይሬክተር ሕብረት አባሆይ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ማህበሩ በምርጫው ጠንካራ የአሰራር ዘዴዎችን ተግባራዊ አድርጓል።

በምርጫ ወቅት በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለመከላከል የተቀናጀ ስራ ማከናወን መቻሉን በመግለፅ በዚህም ሴቶች ያለፍርሀት ድምጽ እንዲሰጡ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።

በ136 የምርጫ ጣቢያዎች ሂደቱን መከታተሉን ጠቁመው፤በዚህም በታዘቡባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ ስርዓት ያለውና ግልፅነቱን ጠብቆ መካሄዱን እንደታዘቡ ተናግረዋል።

ከአካታችነት አንጻርም ጠንካራ አፈጻጸም እንዳለው መመልከት መቻላቸውን ያመላከቱት ዋና ዳይሬክተሯ፤ምርጫው ሰላማዊ መሆኑ ሴቶች ያለስጋት ድምጽ እንዲሰጡ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም