የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን የጋራ ውጤት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን የጋራ ውጤት ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 14/2018 (ኢዜአ)፦ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን በሚሊየን የሚቆጠሩ መራጮችና የሌሎች ባለድርሻ አካላት የጋራ ውጤት በመሆኑ የኢትዮጵያውያን የጋራ ድል ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ገለጹ፡፡
በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ድምጻቸውን የሰጡበት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እስከ እኩለ ሌሊት መካሄዱ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም የምርጫውን አጠቃላይ ውጤት ይፋ ማድረጊያ መርኃ ግብር የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ የሲቪል ማህበራት ወታካዮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላተ በተገኙበት በአዲስ አበባ እያካሄደ ይገኛል።
የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሒደት ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ሁሉ በተለየ መልኩ ከቅድመ ምርጫ እስከ ድህረ ምርጫ በራስ አቅም የተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ አካታችነትን ዋና የትኩረት ማዕከሉ አድርጎ መሥራቱን በመጥቀስ፥ በተለይ የአካል ጉዳተኞች እና የሴቶች የነቃ ተሳትፎ እንደታየበት አመላክተዋል፡፡
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዲጂታላይዜሽን በስፋት ጥቅም ላይ የዋለበት መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም ከ54 ሚሊየን በላይ መራጮች ውስጥ 5 ሚሊየን የሚሆኑት መራጮች እና እጩዎች በዲጂታል ስርዓት መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡
የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ከማለዳው 12 ሰዓት እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ በተሳካ መልኩ መካሄዱን ጠቅሰዋል።
የምርጫው መሳካት የቦርዱ ብቻ ሳይሆን የባለድርሻ አካላት ጥረት ውጤት መሆኑን የጠቀሱት ሰብሳቢዋ፥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውጫዊ ጫናዎችን ተቋቁመው ተንቀሳቃሽና ቋሚ ወኪሎቻቸውን በማሰማራት ክትትል አድንቀዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የመራጮች ትምህርት በመስጠትና የታዘቧቸውን ችግሮች ከስር ከስር ለቦርዱ ሪፖርት በማድረግ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሂደቱን በቅርብ በመከታተል ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ገልጸዋል።
የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትም መረጃዎችን በፍጥነት በማሳወቅና ክፍተቶችን በመጠቆም ረገድ ተቋማዊ ግዴታቸውን መወጣታቸውን አብራርተዋል።
የአፍሪካ ህብረት እና የኢጋድ ዓለምአቀፍ ታዛቢዎች የመጀመሪያ ሪፖርታቸውን ማውጣታቸውንና በቀጣይም የመጨረሻውን እንደሚያቀርቡ ጠቁመው፤ በአዲስ አበባ የሚገኙ ዲፕሎማቶችም የቦርዱን ማዕከልና የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን መጎብኘታቸውን ጠቅሰዋል።
የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዛሬ ይፋ ሲሆን ስኬቱ የአንድ ተቋም ወይም የጥቂት ግለሰቦች ብቻ አይደለም ብለዋል።
ይልቁንም በፀሐይና በዝናብ ሳይበገሩ በትዕግስት ተሰልፈው ድምጻቸውን የሰጡ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ መራጮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የጸጥታ አካላት፣ ታዛቢዎችና የሌሎች ባለድርሻ አካላት የጋራ ጥረት ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።
የምርጫ አስፈጻሚዎች ምርጫው ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ እስከ ፍጻሜው እንዲሳካ በበዓላት ጭምር ቀን ከሌሊት ላደረጉት ትጋት አመስግነዋል።
የአፍሪካ ህብረት እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የምርጫ ታዛቢ ቡድኖች ኢትዮጵያውያን በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር በማሳየት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ስኬታማና ሰላማዊ ምርጫ ማካሄዳቸውን አረጋግጠዋል።
ጠቅላላ ምርጫው በ1 ሺህ 139 ምርጫ ክልሎች ላይ የተካሄደ ሲሆን ከዚህም ውስጥ የ501 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በክልል ምክር ቤት ከ638 የምርጫ ክልሎች ላይ መካሄዱ ይታወሳል።