ቀጥታ፡

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተቋማዊ ገለልተኝነቱን ጠብቆ በህግና መመሪያ መሰረት ብቻ ስራዎቹን አከናውኗል- ሜላትወርቅ ሀይሉ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 14/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተቋማዊ ገለልተኝነቱን ጠብቆ በህግና መመሪያ መሰረት ብቻ ስራዎቹን ማከናወኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሀይሉ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት የማሳወቂያ መርሀ-ግብር በማካሄድ ላይ ነው።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ እና በምርጫው የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች፣ የሀገራት አምባሳደሮች እና የሲቪክ ማህበራት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ምርጫ ቦርድ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አካታችነትን መርህ አድርጎ ስራውን አከናውኗል።

በሀገር ውስጥ በለማ ቴክኖሎጂ የመራጮች እና እጩዎች ምዝገባ መካሄዱን ተናግረዋል።

ቦርዱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሁል ጊዜ ግንኙነት እንዲሁም የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱን ገልጸው፤ ቦርዱ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክር መድረክ ማዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ጠንካራ የሎጂስቲክስ ስራ በመሰራቱ የምርጫ ቁሳቁሶች በጊዜ እንዲደርሱ መደረጉን ጠቁመው፤ ተቋማዊ ገለልተኝነቱን ጠብቆ በህግና መመሪያ መሰረት ብቻ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ተናግረዋል።

የምርጫው ስኬት የበርካታ ባለድርሻ አካላት ውጤት መሆኑን ጠቁመው፤ ህብረተሰቡ በምርጫው ንቁ ተሳትፎ ማድረጉን ተናግረዋል።

ቦርዱ 42 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉበትና በርካታ ሚሊዮን ዜጎች ድምፅ የሰጡበትን ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም አካሂዷል።

የድምፅ መስጫ ሂደት ባልተጠናቀቀባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ድምፅ የመስጠት ሂደትም እስከ ዕኩለ ለሊት 6:00 ሰዓት ድረስ ተራዝሞ መራጮች ድምጻቸውን ሰጥተዋል።

በቦርዱ የምርጫ ዕውቅና የተሰጣቸው ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በምርጫ ታዛቢነት እንዲሁም በመራጮች ትምህርትና ስልጠና ስኬታማ ተሳትፎ አድርገዋል።

የአፍሪካ ህብረት እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የምርጫ ታዛቢ ቡድኖችም ኢትዮጵያዊያን በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር በማሳየት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ስኬታማና ሰላማዊ ምርጫ ማካሄዳቸውን አረጋግጠዋል።

ጠቅላላ ምርጫው በ1ሺህ 139 ምርጫ ክልሎች ላይ የተካሄደ ሲሆን ከዚህም ውስጥ የ501 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በክልል ምክር ቤት ከ638 የምርጫ ክልሎች ላይ መካሄዱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም