ቀጥታ፡

ለሀገራዊ ምክክር የመጨረሻው ምዕራፍ ስኬታማነት የድርሻችንን እንወጣለን -ምሁራን

ወላይታ ሶዶ፤ ሰኔ 14/2018(ኢዜአ)፡- ለሀገር ዘላቂ ሰላምና አንድነት ቁልፍ ሚና ላለው ሀገራዊ ምክክር የመጨረሻ ምዕራፍ ስኬታማነት በምርምር የታገዙ ሃሳቦችን በማቅረብ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።

በሀገሪቱ ያሉ ችግሮችን በውይይት ለመፍታትና ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፣ የተሳታፊዎች ልየታና የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራውን በማጠናቀቅ ወደ ማጠቃለያው ምዕራፍ መሸጋገሩን አስታውቋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ዘውድነህ ቶማስ (ዶ/ር) እንዳሉት የኮሚሽኑ እንቅስቃሴ እንደ ሀገር ላለመግባባት መንስኤ ለነበሩ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጥ ነው።

ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ባሳተፈ መልኩ የሚካሄደው ሀገራዊ ምከክር በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በውይይትና በሰላማዊ መንገድ በመፍታት የጋራ መግባባት ለመፍጠር ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ዩኒቨርሲቲው ምሁራንን ከመመደብ ጀምሮ ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት በተለያየ መንገድ ሲሰራ መቆየቱንም አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያዊያን በችግሮቻቸው ላይ በጋራ መምከራቸው ለሀገር መጽናት፣ ለሰላም፣ ለልማትና በአብሮነት ለመቀጠል ፋይዳው ከፍተኛ በመሆኑ፣ ለምክክሩ የመጨረሻው ምዕራፍ ስኬታማነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል። 

በተለይም በጥናትና ምርምር የታገዙና ለዘላቂ ሰላም አስተዋጾ ያላቸውን ሀገር በቀል እውቀቶች ተጠቅመው የበኩላቸውን እገዛ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ሌሎችም ምሁራን በሀገራዊ ምክክሩ ላይ በንቃት ከመሳተፍ ባለፈ ህብረተሰቡን በማንቃትና ኮሚሽኑን በማማከር ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የዘለቁ አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጥና ሰላምን በዘላቂነት እንደሚያስቀጥል የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራት ማጎልበቻ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ታፋኖ ኡኬ (ዶ/ር) ናቸው።

"ተመካክሮ ልዩነቶችን መፍታት ነገን በተሻለ መልኩ ለመገንባት ያስችላል" ያሉት ምሁሩ፣ እስከዛሬ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ላይ በመሳተፍ የበኩላቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

የምክክር መድረኩ እንዲሳካ በዕውቀትና በምርምር የተደገፉ ሃሳቦችን በማቅረብ የበኩላቸውን ሲወጡ እንደነበር አስታውሰው፣ በቀጣይም ሀገራዊ ምክክሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ለሁሉም ነገር ሰላም ወሳኝ ነው ያሉት ታፋኖ (ዶ/ር)፤ በሀገሪቱ ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሁሉም ዜጎች ንቁ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም ተሳትፎውን ማጠናከር መብቱ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ግዴታውም እንደሆነ ተገንዝቦ ዜጎች ለመጨረሻው ምዕራፍ ስኬት የበኩላቸውን እንዲወጡም አመልክተዋል።

ዜጎች በሀገራዊ ጉዳይ ላይ  በጋራ  መምከራቸው በሕዝቦች መካከል መተማመንን ለመገንባት፣ ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር እና ላለመግባባት መንስኤ ለነበሩ ዋና ዋና ችግሮች ዘላቂና አካታች መፍትሔ ለማምጣት ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በቅርቡ እንዳስታወቁት የምክክሩ የማጠቃለያ መድረክ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ይካሄዳል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም