የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማት የጎርፍ ተጋላጭነትን በመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማት የጎርፍ ተጋላጭነትን በመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 14/2018(ኢዜአ)፦ የወንዝ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማት የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን በመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ።
በመዲናዋ የተገነቡት የወንዝ ዳርቻ እና የኮሪደር የልማት ስራዎች የከተማዋን ውበት እና ዘመናዊነት በማሳደግ አዲስ አበባን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን እያስቻሉ ነው።
የኮሪደር ልማቱና የወንዝ ዳርቻ ልማቱ ቀደም ሲል የወንዝ ዳርቻዎችን ተገን በማድረግ በአስቸጋሪና ለሕይወታቸው በአስጊ ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ በርካታ ነዋሪችንም መታደግ አስችሏል።
በእነዚህ የተቀናጁ የልማት ፕሮጀክቶች አማካኝነት በተለይ በክረምት ወቅት ያጋጥም የነበረውን የጎርፍ ስጋት በመቅረፍ ነዋሪዎች ያለ ስጋት እንዲኖሩ እያስቻለ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳት እና አደጋ ስጋት አመራር ምክትል ኮሚሽነር ደሳለኝ ፉፋ ለአዜአ እንደገለፁት፤ በክረምት ወቅት የሚከሰተውን የጎርፍና አደጋ ለመከላከል ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል።
ኮሚሽኑ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን፣ በከተማዋ የሚገኙ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች እና የጎርፍ መውረጃዎች በቆሻሻ እንዳይደፈኑ የማጽዳትና የመጠገን ስራዎችን በትኩረት እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ነዋሪዎች በወንዞችና በፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮች ላይ ቆሻሻ እንዳይጥሉ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የጎርፍ ተጋላጭ ቦታዎች ተለይተው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የመከላከል እርምጃዎችን በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
የወንዝ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማት ስራዎች የውሃ ማስወገጃ ቱቦዎችን ችግር በመፍታት በክረምቱ ሊከሰቱ የሚችሉ የጎርፍ አደጋ ስጋቶችን በመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
ይህም ለከተማው ነዋሪ እፎይታን የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።