አዲስ አበባ በአረንጓዴ ዐሻራና በኮሪደር ልማት በምሳሌነት የምትጠቀስ የአፍሪካ ከተማ ሆናለች- አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ በአረንጓዴ ዐሻራና በኮሪደር ልማት በምሳሌነት የምትጠቀስ የአፍሪካ ከተማ ሆናለች- አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 14/2018(ኢዜአ)፦አዲስ አበባ በአረንጓዴ ዐሻራና በኮሪደር ልማት ባከናወነቻቸው አስደናቂ ተግባራት በምሳሌነት የምትጠቀስ የአፍሪካ ከተማ ሆናለች ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ‘‘ተስፋን እንትከል’’ በሚል መሪ ሀሳብ የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በይፋ አስጀምሯል።
በመርሃ ግብሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዲሁም ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ዘንድሮ የምናከናውነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ በሆነ መንገድ ባከናወንንበት ማግስት መጀመሩ ልዩ ትርጉም የሚሰጠው እንደሆነ ገልጸዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተከናወኑ ሥራዎች ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ ለዘላቂ ልማት አይተኬ ሚና እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ የተሠራው ታላቅ ሥራ ዓለም አቀፍ እውቅናን ማስገኘቱን ገልጸዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ሥራ በመንግሥት በተሰጠው ቀዳሚ ትኩረት በተቋም እየተመራ መሆኑ ሥራውን ይበልጥ ስኬታማና ውጤታማ እንዳደረገው አብራርተዋል።
አዲስ አበባ ከተማም በአረንጓዴ ልማትና በኮሪደር ልማት ባከናወነቻቸው አስደናቂ ተግባራት በአፍሪካ ደረጃ በምሳሌነት የምትጠቀስ ከተማ እየሆነች መምጣቷን ገልጸዋል።
ሁሉም ዜጋ የተጀመረውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በላቀ ተነሳሽነት በመቀላቀል ለሀገር ዘላቂ ልማት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክትም ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ሀገር አቀፉ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በመዲናዋም ላለፉት ዓመታት ሁሉም ህብረተሰብ በተደራጀ አግባብ እየተሳተፈበት በስኬታማነት ተተግብሯል።
ባለፉት የመርሃ ግበሩ የትግበራ ዓመታት በአዲስ አበባ 90 ሚሊዮን ችግኞች መተከላቸውን ጠቅሰው፥ ይህም አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ የምትመች ከተማ እንድትሆን እያስቻለ ነው ብለዋል።
የከተማዋ የአረንጓዴ ሽፋንም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን መስፈርት ለማሟላት በዕድገት ጉዞ ላይ መሆኑን ያነሱት ከንቲባዋ፥ በ2010 ዓ.ም ከነበረበት 2 ነጥብ 8 በመቶ አሁን ላይ ወደ 24 በመቶ ማደጉን ገልጸዋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ 6 ሚሊዮን ችግኞች ይተከላሉ ብለዋል።
ዘንድሮና በቀጣይ ዓመት በሚተከሉ ችግኞች የከተማዋን የአረንጓዴ ሽፋን 30 በመቶ ለማድረስ ግብ ተቀምጦ እየተሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የምንተክለው ተስፋችንን፣ ራዕያችንን እና ምግባችንን ነው ያሉት ከንቲባዋ ዛሬ ተስፋን እንትከል በሚል መሪ ሀሳብ ችግኞችን የምንተክለው ነገ የተሻለችና ብልጽግናዋ የተረጋገጠች ኢትዮጵያን ለመገንባት መሆኑን አስገንዝበዋል።
ፅዱ፣ ውብና አረንጓዴ ከተማ ለመገንባት ከመትከል ባሻገር የተተከሉ ችግኞችን በየጊዜው መንከባከብና መጠበቅ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ የውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግርማ ሰይፉ ባለፉት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞች ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል።
የከተማዋን ሥርዓተ ምህዳር በመጠበቅና የአረንጓዴ ሽፋኗን በማሳደግ ረገድ የሕዝቡ ተሳትፎ የላቀ ነው ብለዋል።
በዘንድሮው ዓመትም በየአካባቢው ችግኝ የመትከልና የመንከባከብ ሥራን በልዩ ትኩረት ማከናወን ከሁሉም እንደሚጠበቅ አንስተዋል።