በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ዘርፈ ብዙ ጠቃሜታ ያላቸው ችግኞች ተዘጋጅተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ዘርፈ ብዙ ጠቃሜታ ያላቸው ችግኞች ተዘጋጅተዋል
አሶሳ፤ ሰኔ 14/2018 (ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ዘርፈ ብዙ ጠቃሜታ ያላቸው ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻደሊ ሀሰን እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ሀሊፋ በአቡራሞ እና ኡራ ወረዳዎች የሚገኙ የችግኝ ጣቢያዎችን በመጎብኘት ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ዝግጁ የሆኑ ችግኞችን ተመልክተዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ሀሊፋ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚመጡ ጫናዎችን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም ከመፍጠሩም በላይ፣ የግብርናውን ዘርፍ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ እየተሰሩ ካሉ ስትራቴጂካዊ የልማት ስራዎች መካከል ቀዳሚው ነው።
አርሶ አደሩ ከዘርፉ የሚያገኘውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም በመገንዘብ በየዓመቱ በርካታ ችግኞችን እየተከለ እንደሚገኝ የገለጹት ኃላፊው፤ በዘንድሮው መርሃግብርም ለምግብ ዋስትና የሚሆኑ የኢኮኖሚ፣ የደን እና ልዩ ልዩ ጠቃሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል ሙሉ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።
በተለይም በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርት በመስጠት ለአርሶ አደሩ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ መሆን የሚችሉ፣ ዝርያቸው የተሻሻሉ የፍራፍሬ ችግኞች በብዛት መዘጋጀታቸውንም ኃላፊው አክለው ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰዓትም የቦታ ልየታ እና የጉድጓድ ዝግጅት እየተከናወነ እንደሆነ ጠቁመው ሰኔ 16 ቀን 2018ዓ.ም በክልል ደረጃ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር እንደሚጀመር አስታውቀዋል።
የአቡራሞ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አታላይ ደረጀ በበኩላቸው፤ በወረዳው በሚገኙ ከ11 በላይ የችግኝ ጣቢያዎች ከ13 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ለተከላ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ችግኞችን በክላስተር በመትከል የአፈር መሸርሸርን እንዲከላከሉ እና ዘርፈ ብዙ ጠቃሜታ እንዲሰጡ ይደረጋል ነው ያሉት።
በተመሳሳይ በኡራ ወረዳ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን የተናገሩት ደግሞ የወረዳው ግብርና ጽህፈት ኃላፊ አቶ ታጀዲን ሙሐመድ ናቸው።
ከመንግስት በተጨማሪ ግለሰቦች በማህበር ተደራጅተው ችግኝ በማዘጋጀት ውጤታማ ስራ እያከናወኑ መሆናቸውንም አቶ ታጀዲን አስረድተዋል።