ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን ትስስር በማጠናከር የወጣቶችን የሀገር ግንባታ ሚና እያጎለበተ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 14/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር የወጣቶችን የሀገር ግንባታ ሚና እያጎለበተ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በርካታ የሰው ተኮር ተግባራት የሚከናወኑ ሲሆን፣ በተለይም የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን የማካሄድ ልምድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዳበረ መጥቷል።

ከተለያዩ የበጎ ፈቃድ ዘርፎች መካከልም አንዱ የሆነው ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት በትኩረት እየተሰራበት የሚገኝ ዘርፍ ነው።

ይህ መርሃ ግብር ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የበጎ ፈቃድ ስራዎችን ከማከናወን ባለፈ፣ ሀገራቸውን በቅርበት ለማወቅና ለመገንዘብ ትልቅ ዕድል እየፈጠረላቸው ነው።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አሕመድ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ከሁሉም አቅጣጫ የተውጣጡ ወጣቶች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው በጎ ተግባራትን እያከናወኑ ነው።

ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ ወጣቶችን በማቀራረብ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጎልበት የሀገር ግንባታ ገንቢ ሚናቸውን እየተወጡ ነው ብለዋል።

ይህም በወጣቶች መካከል የባህልና እሴት ልውውጥን በመፍጠር ወጣቶች የሀገራቸውን መልክና ልዩ ገጽታዎች የማወቅ ዕድል እየፈጠረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚህም ወጣቶች በጋራ የሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የሚኖራቸውን ሚና ይበልጥ እያጠናከረ መሆኑን ተናግረዋል።

በ2014 ዓ.ም የተጀመረው ይህ መርሃ ግብር፣ ዘንድሮ ለአምስተኛ ጊዜ "በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ 5" በሚል መሪ ሀሳብ ለማከናወን ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።

በሀገር ደረጃ የተጀመረው ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አሁን ላይ በክልሎችና በዞኖች መካከል ልምድ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ እንዳደረገችው ሁሉ በበጎ ፈቃድ ሥራም የበለጸገ ባህልን በመገንባት ለዓለም ተምሳሌት ለመሆን እየሠራች መሆኑን አንስተዋል።

በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ መርሃ ግብርም ወጣቶች በተደመረ አቅም በንቃት በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም