ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ቀጣናዊ ሰላምና ዕድገትን ከማረጋገጥ የሚመነጭ ምክንያታዊ አጀንዳ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 14/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሕጋዊና ታሪካዊ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ቀጣናዊ ሰላምና ዕድገትን ከማረጋገጥ የሚመነጭ ምክንያታዊ ወሳኝ አጀንዳ መሆኑን ምሁራን ገለጹ።

የኢትዮጵያ ረጅሙ የስልጣኔ ታሪክና ሃያልነት ከተፈጥሯዊ የባሕር በር ባለቤትነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑን የታሪክ ድርሳናት ከትበው ያስቀመጡት የአደባባይ ሃቅ ነው።

የሀገር ውስጥ ባንዳና የውጭ ባዕዳን ታሪካዊ ጠላቶች የሸረቡት ሴራም የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ የባሕር በር ባለቤትነት በማሳጣት በሀገር ላይ ኢ-ፍትሐዊ በደል ተፈጽሟል።

በኢትዮጵያዊያን ልብ ለሶስት አስርት ዓመታት ተዳፍኖ እንዳይነሳ ተደርጎ የቆየው የባሕር በር ባለቤትነትም በሀገራዊ ለውጡ ማግስት ወሳኝ አጀንዳ ሆኖ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነትም ከፍተኛ የህዝብ ቁጥርን ከፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት አጣምሮ ለያዘ ሀገር ምላሽን የሚሻ ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ ፍትሐዊ፣ መልክዓምድራዊና ምክንያታዊ ጥያቄ ነው።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ምሁራን፤ ኢትዮጵያ ከተፈጥሯዊና ሕጋዊ የባሕር በር ባለቤትነቷ እንድትገለል የተደረገበት አጋጣሚ የሚያስቆጭ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-አመራርና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ጌትዬ ትርፌ(ዶ/ር)፤ የታሪካዊ ጠላቶችና የውስጥ ባንዳዎች የሴራ ጥምረት የባሕር በር ባለቤትነታችንን እንድናጣ አድርጓል ብለዋል።

የግል ጥቅምን ከማስቀደም የተሻገር ርዕይ ያልነበረው የስልጣን ጥመኛ ቡድን የፈጸመው ክህደት የትውልድን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ በመስጠት በሀገር ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው በደል መፈጸሙን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ ከባሕር በር ባለቤትነቷ በግፍ መነጠሏም፤ በገቢና ወጪ ዓለም አቀፍ የንግድ ተወዳዳሪነትን ከማቀጨጭ ባሻገር ቀጣናውን የሽብርተኞች መፈንጫ ማድረጉን ገልጸዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ በፊትም ለሶስት አስርት ዓመታት ታሪካዊ፣ ሕጋዊና መልክ ዓምድራዊ ይዞታዋ በአጀንዳነት እንዳይነሳ የተደረገበት ትርክትም ዜጎችን አሳዝኖ የቆየ እንደነበር አስረድተዋል።

በሀገራዊ ለውጡ ማግስት ኢትዮጵያዊያን የጋራ አቋም በመያዝ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄን በስትራቴጂክ ብሔራዊ ጥቅም አጀንዳነት ማቅረባቸው የታሪክ ስብራትን የማረም ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ዓለም አቀፍ ዕውቅናን እያገኘ የመጣ የስትራቴጂክ ብሔራዊ ጥቅም ማዕከል መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነትም ቀጣናዊ ትብብርና ጥንካሬን በማጎልበት የሰላም፣ የኢኮኖሚ ዕድገትና የገበያ ትስስር መሰረት መሆኑን አብራረተዋል።


 

በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የፖሊሲና ስትራቴጂ ተመራማሪ ተመስገን ዋለልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የባህር በር ለኢትዮጵያ ቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከስትራቴጂክ የባሕር በር ባለቤትነት መገለሏ ሶስት አስርት ዓመታትን በተሻገረ ዘመን በዜጎች ህይወት ላይ ተፅዕኖ በማሳደር የሎጂስቲክስ ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን አስገንዝበዋል።

በአሁኑ ወቅትም የሃያላኑ ዐይን ማረፊያ በሆነው የቀይ ባሕር ቀጣና ኢትዮጵያዊያን ታሪካዊና ሕጋዊ የባሕር በር ባለቤትነታቸውን ለማስመለስ የሚያደርጉት ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም