የክልሎች ቅኝት በወፍ በረር - ኢዜአ አማርኛ
የክልሎች ቅኝት በወፍ በረር
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 14/2018 (ኢዜአ) ፡-የክልሎች ቅኝት በወፍ በረር
በዚህ ዝግጅታችን በሳምንቱ በክልሎች የተከናወኑ ዋና ዋና ጉዳዮችን በወፍ በረር በመቃኘት ማስታወስ ይሆናል። በመሆኑም በዚህ ሳምንት በሀገራችን ሁሉም ክልሎች ምን ምን ዋና ዋና ጉዳዮች ነበሩ ስንል እንጠይቃለን?
በሳምንቱ ቢሾፍቱ
አዲሱ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ ከአዲስ አበባ 40 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ከባሕር ጠለል በላይ በ1 ሺህ 910 ሜትር ከፍታ ላይ በምትገኘው ቢሾፍቱ ግንባታው በመከናወን ላይ ይገኛል። የኤርፖርቱ ግንባታ ሲጠናቀቅ በዓመት እስከ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገድ የሚያስችል ግዙፍ የልማት ፕሮጀክት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ የቢሾፍቱ ኢርፖርት ኢትዮጵያን ከዓለም ቀዳሚ የአቪዬሽን ማዕከላት ተርታ ለማሰለፍ የሚያስችል ታሪካዊ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ሳምንት ሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በስፍራው በመገኘት የግንባታውን ሂደት የተመለከቱ ሲሆን ግንባታውን በተያዘው ጊዜ ለማጠናቀቅም ሌሊትና ቀን በከፍተኛ ጥረት እየተገነባ ይገኛል ብለዋል።
በእለቱም የ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር በቢሾፍቱ ያስጀመሩ ሲሆን ዘንድሮ የተያዘውን የ8 ቢሊዮን ችግኞች የመትከል ግብ ለማሳካት በሚደረገው ንቅናቄ ኢትዮጵያውያን ለተግባራዊነቱ እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)፤ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ጎሮ ወረዳ በመገኘት የዘንድሮውን የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያስጀመሩትም በዚሁ ሳምንት ነበር። በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክትም ሀገራችንን በጋራ ማንሳት የምንችለው አንዳችን ለሌላችን እጃችንን ስንዘረጋ ብቻ ነው! ስለሆነም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በዚህ ሥራ እንዲሳተፍ ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል።
የሀገር መከታና የህዝብ አለኝታ
የሀገር መከላከያ ሰራዊት የህዝብ ወገንተኝነቱንና እና አለኝታነቱን በተግባር ማሳየቱን ቀጥሎበታል። ሰራዊቱ በጦር ሜዳ ጠላትን ድል ከመንሳት ባለፈ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በላቀ ደረጃ የሚወጣ ህዝባዊ ሰራዊት መሆኑን አሳይቷል። የሀገር መከላከያ ሰራዊት 403ኛ መከታ ኮር የተመሰረተበትን 4ኛ ዓመት በዓል በተለያዩ ተላላቅ መርሃ ግብሮች ባከበረበት ወቅት በሰሜን ጎንደር ዞን የ"ጭና ሰማዕታት መታሰቢያ ጤና ጣቢያ" ገንብቶ ለአካባቢው ማህበረሰብ አስረክቧል።
በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የሰራዊቱ የጀግንነት ታሪክ እንደ ውቅያኖስ የማይነጥፍ ከመሆኑም በላይ፣ በጭና ግንባር የተቀዳጀው ድል የጠላትን ፖለቲካዊና ወታደራዊ አቅም ሙሉ በሙሉ የሰበረ የድል ማህተም ነው ብለዋል።
ለልማት- የሃይል አማራጭን ማስፋት
በኢትዮጵያ ከከተማ እስከ ገጠር የተሰናሰለ የሃይል ልማትን በማስፋት አማራጭ የሃይል አቅርቦት ልማት ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በዚህ ሳምንትም በሲዳማ ክልል ሸበዲኖ ወረዳ ከ312 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት የሚያስችል የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ለመገንባት መሰረተ ድንጋይ ተቀምጧል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሡልጣን ወሊ (ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት የመውጣትና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ጥረት በተቀናጀ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። ለዘላቂ ልማትና ለዜጎች ተጠቃሚነት የሃይል አማራጭን የማስፋት ስራ ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን አንስተዋል።
በምርታማነት የምግብ ስርዓት ችግርን መፍታት
በኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት ችግርን ለመፍታት እስከ ታችኛው መንግስታዊ መዋቅር ድረስ የሚዘልቁ የተለያዩ ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። በዚሁ መሰረትም በምግብ ስርዓት አለመስተካከል የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ገልጿል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በተገኙበት በክልሉ ስርዓት ምግብ ሽግግርና የቀዳማዊ ልጅነት ልማት ፍኖተ ካርታ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሄዷል።
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ችግር ፈች ምርምር
ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በምርምር ሥራዎችና በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመረውን ቅንጅታዊ አሰራር አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጸውም በዚህ ሳምንት ነው። በዩኒቨርሲቲው በምርምር ፕሮጀክቶች እና በማህበረሰብ አገልግሎቶች የተከናወኑ ተግባራትን ለመገምግምና ቅንጅታዊ ሥራን ለማጠናከር ያለመ መድረክም አካሄዶ ነበር።
መድረኩ በተለይ ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶችን እውን ለማድረግና ዓለም አቀፍ ዕድሎችን አስፍቶ ለመጠቀም የተመራማሪዎችን አቅም ማሳደግ ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ ከ84 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ 54 የምርምር ሥራዎችን እንዲሁም 70 የማህበረሰብ አገልግሎቶችን ማከናወኑን ጠቁመዋል።
በቀብሪ በያህ ከተማ የወጣቶች የልማት ተጠቃሚነት
በሶማሌ ክልል የልማትና የምርታማነት አጀንዳዎች በውጤታማነት ቀጥለዋል። የወጣችንና አጠቃላይ የክልሉን ህዝብ የልማት ፍላጎት መሰረት አድርገው እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ ነው። በዚሁ መሰረት በክልሉ ፋፈን ዞን ቀብሪ በያህ ከተማ በማህበር ተደራጅተው ሥራ የፈጠሩ ወጣቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አብዲከሪን መሀመድ እና ጓደኞቹ በማህበር ተደራጅተው በዶሮ እርባታ በመሰማራት በሌማት ትሩፋት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ገልጸዋል። ሥራውን ከጀመሩ ወዲህ ራሳቸውን ከመቻል ባለፈ ለሌሎች ወገኖችም ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ ይናገራሉ። እንደ አጠቃላይ በሶማሌ ክልል ሰው ተኮር የልማት ስራዎች በተጠናከረ መልኩ ቀጥለዋል።
የበጀት ክለሳ
በዚሁ ሳምንት የሐረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የ2018 የበጀት ዓመት የ11 ወራት እቅድ አፈጻጸም መነሻ በማድረግ የቀረበለት የበጀት ክለሳ አፅድቋል። ካቢኔው በክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ አማካኝነት የቀረበለትን ከ301 ሚሊየን 693 ሺህ 178 ብር የበጀት ክለሳ ነው ተወያይቶ ያፀደቀው። የበጀት ክለሳው በተለይም የፊስካልና ፋይናንሻል አፈፃፀማቸው ዝቅተኛ የሆኑ ፕሮጀክቶችን በመለየት የላቀ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ ላላቸውና የበጀት እጥረት ላጋጠማቸው ጉዳዮች የሚውል ነው ተብሏል።
የአንድ ማዕከል አገልግሎት
ኢትዮጵያ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮቿን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ልትሰጠው እየተጋች ነው። ለዚህ ዋና ማሳያው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ነው። ማዕከሉ በሁሉም የሀገሪቷ አካባቢዎች በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ይገኛል። የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በኮንታ ዞን የተገነባውን ኮንታ መሶብ የአንድ ማዕከል መርቀው በይፋ አገልግሎት አስጀምረዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል በተበታተነ ሁኔታ ይሰጡ የነበሩ የመንግሥትና የማኅበራዊ አገልግሎቶችን በአንድ ጣሪያ ሥር በማሰባሰብ ለዜጎች ፈጣን፣ ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው። የኮንታ ማዕከልም ሕዝቡ ከቢሮ ወደ ቢሮ በመዘዋወር የሚያጠፋውን ጊዜ፣ ወጪና እንግልት በእጅጉ በመቀነስ ጥራት ያለው፣ ቀልጣፋና ተደራሽ አገልግሎት እንዲያገኙ ያግዛቸዋል ተብሏል።
የስደተኞች መጠጊያ- ኢትዮጵያ
የተለያዩ ሀገራት ስደተኞች መጠጊያ የሆነችው ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኡራ ወረዳ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ተከብሯል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ክልሉ የተለያዩ ሀገራት ስደተኞችን ከመቀበል ባለፈ ስደተኞችን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
በክልሉ አራት መጠለያ ጣቢያዎች ላይ ከ112 ሺህ በላይ ስደተኞች እንደሚገኙ ገልፀው፥ ስደተኞች ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ጠንካራ መስተጋብር በመፍጠር በአብሮነት እየኖሩ ነው ብለዋል። ስደተኞች የውሃ፣ የትምህርት የጤናና ሌሎች የመሠረተ ልማቶችን ከተቀባዩ ማህበረሰብ እኩል ተጠቃሚ መሆናቸው የኢትዮጵያን ስደተኞች አያያዝ የተሻለ ተሞክሮ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ጋምቤላ
የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አባላት በመጪው የህዝብ ውክልና ስራ ስምሪት ወቅት የሚያከናውኗቸውን ተግባራት በተመለከተ የኦሬንቴሽን ፕሮግራም አካሂዷል። የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ ጁል ናንጋል፣ የህዝብ ውክልና ተግባር የምክር ቤት አባላት ዋና ሃላፊነት መሆኑን ገልፀው፣ አባላቱ ወደ ህዝቡ በመቅረብ የህብረተሰቡን ፍላጎት፣ ችግርና አስተያየት በአግባቡ በማሰባሰብ ለመንግስት አካላት ማድረስ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ምክትል አፈ ጉባኤው እንዳሉት፣ የህዝብ ውክልና ስራ በዜጎችና በምክር ቤቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እና የህዝብ ተሳትፎን ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ አባላቱ በተሰጣቸው ኃላፊነት ትጋትና ቁርጠኝነት እንዲሰሩ አሳስበዋል።
ድሬደዋ
ድሬደዋ የመስኖ ግንባታ። 'በቆላማ አከባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራም' በሁላሁሉል ገጠር ቀበሌ ውስጥ የከርሰ ምድር ውሃን በመጠቀም የተሰሩ የንፁህ መጠጥ ውሃና የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች፥ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብረሃም በላይ (ዶ/ር) በተገኙበት ተመርቋል። የመስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ሚኒስትር አብረሃም በላይ (ዶ/ር) እና የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፤ ግድቡን በመረቁበት ወቅት ከምንም በላይ ለሰው ልጆች ህይወት እጅግ አስፈላጊ የሆነውና፥ የአስተዳደራችን የገጠር ነዋሪ ህብረተሰብ መሠረታዊ ፍላጎትና የረጅም ዘመናት ምኞት የነበረውን፥ የውሃ ጥያቄ በጋራ ርብርብ መመለስ መቻል የሚሰጠው ደስታ እጅግ ልዩ ነው ብለዋል ከንቲባው።
የድሬዳዋን ማህበረሰብ የምግብ ሉኣላዊነት የማረጋገጥ፣ አርሶአደሩ ነዋሪ ከራሱ አልፎ ለገበያ በማቅረብ ኑሮውን እንዲያሻሽል እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የመስኖ ልማት ሥራዎችን እንዲያከናውን በማገዝ ረገድ ቀጣይነት ያለው ስራ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
አፋር
ሳምንቱ በአፋር ክልል በማህበረሰብ ተጠቃሚነት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ ያሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ወጣቶች፣ ባህልና ስፖርት ቢሮ ያስታወቀበትም ነበር።
የአፋር ክልል አብዛኛው ማህበረሰብ ከፊል አርብቶ አደርና አርብቶ አደር በመሆኑ፣ በየዓመቱ የሚከናወኑ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎቶች የአካባቢውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክፍተቶች ለመሙላት ትልቅ ሚና አላቸው። በተለይም የአየር ንብረት መለዋወጥ፣ የውሃ እጥረት እና አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎችን ተቋቁሞ ዘላቂ ልማት ለማምጣት የወጣቶችና የህብረተሰቡ የተቀናጀ አቅም ወሳኝ ግብዓት ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።
ማጠቃለያ
ሳምንቱ በሁሉም ክልሎች መደበኛ የልማት፣ የማህበራዊ እና የሰላም ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው የቀጠሉበትም ነበር። በሁሉም ክልሎች የስድስተኛ እና ስምንተኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና በተሳካ ሁኔታ ተካሄዷል። በተመሳሳይ የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ዝግጅት በሁሉም ክልሎች እየተከናወነ ይገኛል።