የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማትና የማስፋፊያ ሥራዎች በርካታ ዜጎችን የሀይል ተጠቃሚ አድርገዋል - ኢዜአ አማርኛ
የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማትና የማስፋፊያ ሥራዎች በርካታ ዜጎችን የሀይል ተጠቃሚ አድርገዋል
ሀዋሳ፤ ሰኔ 14/2018(ኢዜአ):-የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት እና ተደራሽነትን በማስፋፋት የዜጎችን የሀይል ፍላጎት ለመመለስ በተከናወኑ ተግባራት በርካቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሲዳማ ክልል ሆኮ ወረዳ ከጸሐይ ሀይል 525 ኪሎ ዋት ሀይል የሚያመነጭ ፕሮጀክት ተመርቋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለጹት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ዜጎችን በኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራት ተከናውነዋል።
ባለፉት ዓመታት የተለያዩ አማራጮች በመጠቀም የኤሌክትሪክ ሀይል መሰረተ ልማት እና ተደራሽነትን በማስፋፋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያስቻሉ ሥራዎች መከናወናቸውን አስታውሰዋል።
በየዓመቱ ከዋናው የኤሌትሪክ ሀይል የሚጠቀሙ ሰዎችን ቁጥር ማሳደግን ጨምሮ አማራጭ ታዳሽ ሀይልን ለኤሌክትሪክ ሀይል ፍላጎት ለመጠቀም የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋፋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማትና ተደራሽነትን በማስፋፋት እያደገ የመጣውን የሀይል ተጠቃሚነት ፍላጎት ለመመለስ በተደረጉ ጥረቶች በርካቶች ተጠቃሚ መሆናቸውንም ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል።
ለእዚህም ቀደም ሲል ከዋናው የኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚዎች ቁጥር በዓመት 240 ሺህ እንደነበር አስታውሰው በአሁኑ ወቅት ከ600 ሺህ በላይ ማድረስ መቻሉን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ባለፉት አራት ዓመታት ከ85 ሺህ በላይ የቤተሰብ ሶላርን ማሰራጨት ተችሏል ያሉት ኢንጂነር ሱልጣን (ዶ/ር)፣ ከ2 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማትንም ተጠቃሚ በማድረግ የዜጎችን የማህበራዊ አገልግሎት ያሻሻሉ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።
በተጨማሪ በቤተሰብና በተቋማት ደረጃ የኢነርጂ ቆጣቢና ባዮ ማስ ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋት በርካታ ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል።
በቀጣይም የኤሌክትሪክ ሀይል ተደራሽነትን ሽፋንን ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎችን በማጠናከር የተያዘውን ግብ ለማሳካት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
በሀገሪቱ ፍትሀዊ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲኖር በዋና መስመርና ከዋና መሰመር ርቀው የሚገኙ አካባቢዎችን ያካተተ ሥራ እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የፕሮጀክት ፖርትፖሊዮ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክንፈ ነጋሽ ናቸው።
እሳቸው እንዳሉት በተለይም ከዋናው መስመር ርቀው የሚገኙ ገጠራማ አካባቢዎችን እንደ ሶላር ያሉ አማራጭ የታዳሽ ሀይል በመጠቀም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
በዚህም እንደ ሀገር 97 ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ መሆናቸውን ጠቁመው፣ እስካሁን ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት በበቁ 43 ፕሮጀክቶች በርካታ ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል።
የኤሌክትሪክ ሀይል መስፋፋት ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማሳደግንና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን ለማነቃቃት ጉልህ ሚና እንዳለው የተናገሩት ደግሞ የሲዳማ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ሃላፊ ኢንጂነር ከበደ ጋኖሌ ናቸው።
በክልሉም በመደበኛና በአማራጭ ታዳሽ ሀይል በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ፕሮጀክቶች ተከናውነዋል ብለዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡት በሆኮ ወረዳ የሆዲ ቦኩ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ አለሙ ሎጊታ በበኩላቸው በመብራት እጦት በጨለማ ይኖሩ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚ በመሆናቸው ችግራቸው መፈታቱን ተናግረዋል።
በአካባቢያቸው የኤሌክትሪል ሀይል ተደራሽ መሆኑን ተከትሎ የጤናና የትምህርት አገልግሎትን በአግባቡ እያገኙ መሆናቸውንም ተናግረዋል።