ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና ምላሽ ለመስጠት ወሳኝ ነው-የሀገር ሽማግሌዎች

ሰመራ፣ሰኔ 14/2018(ኢዜአ)፡-ሀገራዊ ምክክሩ የሀገሪቱን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታትና ምላሽ ለመስጠት ወሳኝ በመሆኑ ሂደቱ በውጤታማነት እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚያደርጉትን ሁለንተናዊ ድጋፍ ይበልጥ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአፋር ክልል የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።

በኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩና ለግጭት መንስኤ የሆኑ መሠረታዊ የፖለቲካና የአስተሳሰብ ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት፣ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። 

ይህ ሀገራዊ የምክክር ሂደት በሕዝቦች መካከል መተማመንን ለመገንባት፣ ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር እና ለተወሳሰቡ የሀገሪቱ ችግሮች ዘላቂና አካታች መፍትሔ ለመፈለግ ያለመ ትልቅ ታሪካዊ መድረክ ነው።

በአሁኑ ወቅት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የምክክሩን የማጠቃለያ መድረክ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚያካሄድ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ መግለፃቸው ይታወሳል።

የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የባሕል መሪዎች በማኅበረሰቡ ዘንድ ያላቸው ተሰሚነትና የቆየ የግጭት አፈታት ሥርዓት ዕውቀት፣ ለዚህ ምክክር ስኬታማነት እጅግ ወሳኝ እንደሆነም ይታመናል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአፋር ክልል የሀገር ሽማግሌዎች እንዳሉት፤ ሀገራዊ ምክክሩ ለሀገሪቱ ዘላቂ ችግሮች መፍትሔ የሚገኝበት ወሳኝ መድረክ ነው።

በመሆኑም ሂደቱ በውጤታማነት እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚያደርጉትን ሁለንተናዊ ድጋፍ ይበልጥ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው  የአገር ሽማግሌዎቹ የተናገሩት።

ከሀገር ሽማግሌዎቹ መካከል አቶ ዶላት ሃመዱ፤ እንደ ሀገር ሽማግሌነታቸው በሀገራዊ ምክክሩ ላይ ለመሳተፍ በመቻላቸው መደሰታቸውን ገልጸው፣ ኮሚሽኑ እያከናወነ ያለው ሥራ የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።

በአፋር ባህልና ወግ መሠረት ማንኛውንም የተፈጠረ ችግር በውይይትና በንግግር መፍታት ትልቅ ተቀባይነት እንዳለው ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ደግሞ ሀገራችን ካጋጠሟት ችግሮች እንድትወጣ ይህ ሀገራዊ ምክክር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

የምክክር ሂደቱ ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከትልቅ እስከ ትንሹ፣ ከሴት እስከ ወንዱ ማኅበረሰቡን ስናስገነዝብ የቆየንበት ጉዳይ በመሆኑ፤ ሂደቱ ውጤታማና ፍሬያማ እንዲሆን የራሴን ድርሻ እወጣለሁ ብለዋል።


 

ሌላኛው የሀገር ሽማግሌ አቶ አዳሂስ ዓሊ በበኩላቸው፤ የሀገሪቱ ተደራራቢና ተያያዥ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በጀመረው የውይይት መስመር ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ የተጣለበትን የሕዝብ አደራና ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ መሆኑን የገለጹት አቶ አዳሂስ፤ መላውን ማኅበረሰብ በየደረጃው በማሳተፍ በዋና ዋና የልዩነት አጀንዳዎች ላይ ማወያየት መቻሉን አብራርተዋል።

በአፋር ማኅበረሰብ ዘንድ ለውይይትና ለምክክር ትልቅ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ያብራሩት አቶ አዳሂስ፤ በክልል ደረጃ የተከናወኑት የሕዝብ ውይይቶችም ውጤታማ በሆነ መልኩ መካሄዳቸውን አስታውሰዋል።

የተጀመረው የምክክር መድረክ ለሀገሪቱ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ወሳኝ መሆኑን ሌላኛው የሀገር ሽማግሌ አቶ ሐሰን ዱብኖ ተናግረዋል።


 

ምክክሩ የሕዝቦች ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ የሚያገኝበት መድረክ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በጋራ በመሆን ሀገራዊ አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ማንኛቸውም ጉዳይ በውይይትና በመመካከር ሊፈታ እንደሚችል የጠቆሙት የሀገር ሽማግሌው፤ በምክክሩ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ሁሉ እንደሚያግዙ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም